ጥር ፲፰ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ዓ.ም
“”””””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
******
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ አገር አቀፍ የስብከተ ወንጌልን አገልግሎት በተጠና፣ተቋማዊ በሆነና ለውጥ ሊያመጣ በሚያስችል መልኩ ማከናወን የሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከሚመለከታቸው አካላትና ከስባቱ ክፍላተ ከተማ ሥራ አስኪያጆችና የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊዎች ጋር ጥር ፲፮ ቀን ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መሰብሰቢያ አዳራሽ የምክክር መድረክ አካሔደ።

በውይይት መድረኩ ላይ የመምሪያው ዋና ኃላፊ መ/ሰ ቆሞስ አባ ቃለጽድቅ ሙሉጌታ ዶ/ር ስብከተ ወንጌል የቤተክርስቲያናችን ዋነኛ ተልዕኮና ተቀዳሚ ሥራ ሞሆኑን አውስተው ይህን ተቀዳሚ የቤተክርስቲያናችን ሥራ በቂ መምህራንና ምቹ ሁኔታዎች ባሉበት ሁኔታ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት በሚያስችል መልኩ ሥራውን ማከናወን አለመቻል በእጅጉ አሳዛኝ መሆኑን ጠቁመው ዘመኑን በሚመጥንና በሚዋጅ መልኩ የስብከተ ዘንጌል ሥራችንን በተጠናና ውጤት ሊያመጣ በሚችል አግባብ በማከናወን ስኬታማ ሥራ ለመሥራት መዘጋጀት ይኖርብናል ብለዋል።

የመምሪያው የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ በጉባኤው ላይ በመገኘት ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክትም ቤተክርስቲያን የሰጠችንን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት በስብከተ ወንጌል ዘርፍ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት መወያየት፣ችግሩን ማወቅና ለችግሩ መፍትሔ መስጠት የሚያስችል ስልቶችን ቀይሶ በመስራት ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ እንደሚቻል ጠቁመው ቤተክርስቲያናችን የምሁራንና የሰባኪያነ ወንጌል እጥረት የሌለባት ተቋም ስለሆነች ይህኔን የመሰለ የውይይት መድረኮችን በማመቻቸት በችግሮቹና በመፍትሔዎቹ ዙሪያ በመምከር አገር አቀፉን የስብከተ ወንጌል አገልግሎታችንን ለማስፋፋትና ለማጠናከር በጋራ መስራት ይኖርብናል ብለዋል።

በውይይት መርሐ ግብሩ ላይ የተሳተፉት የሥራ ኃላፊዎችም የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱን ለማጠናከርና ለማስፋፋት ይህን የመሰለ የውይይት መድረክ ማመቻቸት ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው አገር አቀፉን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት መርሐ ግብርን ውጤታማ ለማድረግ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቅርብ ጊዜ ውስጥም አገር አቀፍ የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን ለማስፋፋትና ታላላቅ ጉባኤዎችን በማከናወን የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱን በተጠናከረ መንገድ የማከናወን ሥራ መሰራት እንደሚጀምርም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ገልጿል።በተጨማሪም የዚህ ምክክር ዓላማ ጥር ፴ እና የካቲት ፩ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም ለሚካሔደው አገር አቀፍ የስብከተ ወንጌል ጉባኤ ግንዛቤ መፍጠር መሆኑንም መምሪያው ጨምሮ አስታውቋል።