እነሆ በውኃ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ማን ነው?

ይህ ቃለ ሃይማኖት ከኢትዮጵያዊው ጃንደረባ አንደበት የተሰማ ድምፅ ነው (ግብ.ሐዋ. 8፥39)። ምሥራቅ አፍሪካዊቷ ሀገራችን ቅድስት ኢትዮጵያ በኖረችባቸው ብዙ ሺህ ዓመታት ሁሉ መሠረታዊ ታሪኳ ከአምልኮተ እግዚአብሔር ጋር የተሳሰረ ስለሆነ ሀገረ እግዚአብሔር በመባል ትታወቃለች።

በቀዳማዊ ምኒልክ አማካኝነት በንጉሡ በዳዊት ልጅ በሰሎሞን ዘመን ጽላተ ሙሴን ከነመስዋዕቱ፥ ሕገ ኦሪትን ከነሥርዐቱ ተቀብላ ሀገራችን ኢትዮጵያ አምልኮተ እግዚአብሔርን በዘመነ ብሉይ ስትፈጽም እንደነበር በቅዱስ መጽሐፍ ተመዝግቧል (1ነገ. 10፥9)። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመዋዕለ ስብከቱ በዚህ ንስሓ በማይገባ ትውልድ ንግሥተ አዜብ ትፈርድበታለች፤ ከምድር ዳርቻ የሰሎሞንን ጥበብ ለማየት መጥታለች ብሎ ሀገራችንን ጠቅሷታል (ማቴ. 12፥40)።

ቀደምት ኢትዮጵያውያን አባቶቻችንም ጣዖት ያላመለኩ፥ በሕገ ኦሪት በአምልኮተ እግዚአብሔር የኖሩ ስለነበር ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም እየሄዱ ይሰግዱ፥ ሥርዐተ ኦሪትን፥ ሕገ ኦሪትን ይፈጸሙ ነበር። በዚያም መሠረት ነው «ወሖረ ኢየሩሳሌም ይስግድ ወእንዘ ይገብእ ነበረ ዲበ ሠረገላሁ ያነብብ መጽሐፍ ኢሳይያስ ነቢይ – የኢትዮጵያ ሰውም ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር፤ ሲመለስም በሠረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር። መንፈስ ቅዱስ ፊልጶስን ወደዚህ ሠረገላ ቅረብና ተገናኘው አለው» (ግብ.ሐዋ. 8፥28-32)።

ፊልጶስም መንፈስ ቅዱስ በነገረው መሠረት ወደ ሠረገላው ሲቀርብ ኢትዮጵያዊውን መጽሐፈ ኢሳይያስን ጸሪቀ ሐዲስ በመባል የሚታወቀውን ምዕራፍ ሃምሳ ሦስትን ሲያነብ አገኘው። ፊልጶስም በውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን አለው። ያለ መምህር እንዴት እረዳዋለሁ፥ እባክህ ነቢዩ ስለምን እንደሚናገር አስረዳኝ አለው። ፊልጶስም ለጃንደረባው ኢትዮጵያዊ ወንጌል ሰበከለት።

በመላው ዓለም ወንጌልን እንዲሰብኩ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የታዘዙትን ሐዋርያት እኛን ኢትዮጵያውያንን ያገኙን ጣዖት እያመለክን አይደለም፤ ብሉይ ኪዳንን እያነበብን፥ እግዚአብሔርን እያመለክን እንጂ። በብሉይ ኪዳን በሕገ ኦሪት የለሰለሰ እርሻ ስለነበር ባለመቶ አድርጎ የወንጌልን ፍሬ ለማብቀል ጊዜ አልወሰደበትም። ከፊልጶስ ጠቅላላ ነገረ ክርስቶስን፥ ቅዱስ ወንጌልን ከሰማና ከተማረ በኋላ «ውኃ ይኸውና፥ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድን ነው» ብሏል።

ሐዋርያው ቅዱስ ፊልጶስም «ከአመንክ ተፈቅዷል» አለው። ኢትዮጵያዊው ጃንደረባም «ወይቤ አነ አአምን ከመ ኢየሱስ ክርስቶስ ወልዱ ለእግዚአብሔር — ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ» አለ፤ ከዚያም በኋላ ሠረገላው እንዲቆም ሆነ። ወወረዱ ኅቡረ ኀበ ማይ ፊልጶስ ወውእቱ ኅጽው ወአጥመቆ እማይ ወእመንፈሰ እግዚአብሔር — ፊልጶስና ጃንደረባውም ወደ ውኃው ወረዱ፤ አጠመቀውም።

ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ የተናገረው የእምነት ቃል እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው እኔን ማን ይለኛል ብሎ በተናገረ ጊዜ፦ «ሌሎች ሙሴ ነህ፥ ኤልያስ ነህ፥ ዮሐንስ መጥምቅ ነህ፥ ወይም ከነቢያት አንዱ ነህ» ይሉሃል አሉ። ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ «አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ» ብሏል (ማቴ. 16፥16-20)። እንዲሁም ሐዋርያው ናትናኤል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከበለስ ሥር አየሁት ሲለው፥ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፥ ወልድ ነህ በማለት እምነቱን ገልጿል (የሐዋ.ሥራ 1፥48-53)። ሐዋርያው ወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስም በወልድ የሚያምን የዘለዓለም ሕይወት አለው ብሏል።

ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ከፊልጶስ ቅዱስ ወንጌልን ተምሮ ሃይማኖቱን ሲገልጽ፦ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ ብሎ ሃይማኖቱን ተናግሮ፥ መስክሮ በሐዋርያው እጅ ተጠምቋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በደመ ክርስቶስ፥ በትምህርተ ሐዋርያት የተመሠረተች ጥንታዊት፥ ሐዋርያዊት ናት የምትባለውም ስለዚህ ነው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት «ሑሩ ወመሐሩ ኵሎ አሕዛበ ወእንዘ ታጠምቅዎሙ በሉ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ መሐርዎሙ ይዕቀቡ ኵሎ ዘአዘዝኩክሙ ወናሁ አነ እሄሎ ምስሌክሙ በኵሉ መዋዕለ እስከ ሕልፈተ ዓለም — እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ፥ ያዘዝኋችሁን ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችሁ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ» (ማቴ. 18፥19-20) ሲል መሠረታዊውን የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮና ሥራ ለደቀ መዛሙርቱ ተናግሯል።

በዚህ በጌታችን በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምላካዊ ትእዛዝ መሠረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምንጊዜም ሥራዋና ተልዕኮዋ ቅዱስ ወንጌልን ማስተማር፥ ማጥመቅ፥ ማቍረብ ነው። ቤተ ክርስቲያን ሰፋች፥ ጠነከረች፥ ታነጸች የሚባለው ብዙ ቍጥር ያላቸው ሰዎች እያመኑ ተጠምቀው የክርስቶስ ተከታዮች ሲሆኑ ነው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይት በተነሣ በ40 ቀኑ ወደ ሰማይ ሲዐርግ እጆቹን በቅዱሳን ሐዋርያት ላይ ዘርግቶ ባርኮ ሥልጣነ ክህነትን ለሐዋርያት ሰጥቷል (ሉቃ. 24፥50)። ቅዱሳን አበው ሐዋርያት ያጠመቁት፥ ከጌታ በምድር የሠራችሁት በሰማይ የታሠረ ነው፤ በምድር የፈታችሁት በሰማይ የተፈታ ነው ተብሎ በተሰጣቸው ሥልጣነ ክህነት ነው። ቅዱሳን አበው ሐዋርያት ከጌታ ያገኙትን ሥልጣነ ክህነት በአንብሮተ እድ አስተላልፈዋል (ግብ.ሐዋ. 6፥1-6)። ይህም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምትመራበት ሥልጣነ ክህነት ከአበው ወደአበው ሲተላለፍ ይኖራል (1ጢሞ. 5፥22)።

እንግዲህ ከላይ በተገለጸው መሠረት የሥላሴን ልጅነት ከሚያስገኘው ከመርገመ ኀጢአት፥ ከዲያብሎስ ቁራኝነት የሚያላቅቀው የክርስትና ጥምቀት ሥልጣነ ክህነት ባለው ካህን መፈጸም አለበት። ጥምቀተ ክርስትና ለአማኙ የሚፈጸመው በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ብቻ ነው። የተጠመቀ ሰው በዕለቱ መቍረብ አለበት። ስለ ጥምቀተ ክርስትና አፈጻጸም ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 3 ከቍ. 20-30 እንዲህ ይላል፦

«ጥምቀትሰ ሥርዕ ላዕለ ዕደው ወአንስት ገውሶሙ ወዐቢዮሙ በእንተ ዘይቤ እግዚአብሔር ሎቱ ስብሐት ዘኢተወልደ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ ኢይሬእያ ለመንግሥተ እግዚአብሔር — ጥምቀትስ ለወንዶችም ለሴቶችም፥ ለትልቁም ለትንሹም የታዘዘ፥ የተገባ ነው። ክብር ይግባውና ጌታችን በወንጌል ከውኃና ከመንፈስ ያልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት አያይም ስለአለ» ይልና፤ አያይዞም ስለዚህ ይህ አንቀጽ አፈጻጸሙ ሲናገር «ኢያጥምቅ ዘእንበለ ኤጲስቆጶስ አው ቀሲስ ወዲያቆናት ይትልአኩ ምስሌሆሙ — ከኤጲስ ቆጶስ ወይም ከቄሱ በስተቀር ማንም አያጥምቅ፤ ዲያቆናት ግን ከእነርሱ ያገልግሉ፤ ይላላኩ።» «ወለእመቦ ብእሲ ዘተወክፈ ጥምቀተ እምአላውያን ኢኮነ ውእቱ ምእመነ — ከመናፍቃን ጥምቀትን የተቀበለ ሰው ቢኖር አማኝ የክርስቶስ ተከታይ አይደለም ይላል»፤ ይቀጥልና፦ ሴቶች ወንዶችን ክርስትና አያንሱ፤ ወንዶች ወንዶችን፥ ሴቶች ሴቶችን ያንሱ በማለት ያስረዳል።

ወንጌላዊው ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ከጌታ ጎን በፈሰሰው ማየ ገቦ አማኞች ተጠምቀው ልጅነት እንደሚያገኙ በሀብተ መንፈስ ቅዱስ እንደሚከብሩ ሲገልጽ፦

«አኮ በማይ ባሕቲቱ አላ በማይኒ ወለአምኒ ወበመንፈስ ውእቱ ዘስምዐ ይከውን ከመ መንፈሰ ጽድቅ፥ ሠለስቲሆሙ አሐዱ እሙንቱ — በውኃ ብቻ አይደለም የዕለት ጽንስ በመሆን በደማዊ አካል በመገለጽ የባሕርይ አምላክ እንደሆነ በሚመሰክር በመንፈስ ቅዱስም ነው እንጅ» (1ዮሐ. 5፥6-10)። ይህም ማለት ካህናት ዕለት ዕለት በስመ ሥላሴ በሚለውጡት ማየ ገቦ፥ በሚያሰጡት ሀብተ መንፈስ ነው። በደምኒ ማለት በደመ ላሕም፥ በደመ በግዕ ሳይሆን በራሱ ክቡር ደም በደመ ገቦ፥ በመንፈሰ ረድኤት ሳይሆን በመንፈሰ ልደት ነው።

ሠለስቲሆሙ አሐዱ ማለት ደግሞ ሦስቱ እንደ ሰው ይቀበልቸዋልና በአንድ ቄስ እጅ ሲሰጡ ይኖራሉ። አንድ ክብረ መንግሥተ ሰማያትን ያስገኛሉ፥ በማለት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ይተረጒማሉ።

ታላቁ ሐዋርያ መምህረ አሕዛብ ቅዱስ ጳውሎስ «ከመ ትኩን አሐደ ሥጋ ወአሐደ መንፈስ በከም ተጸዋዕክሙ ለአሐዱ ተስፋክሙ አሐዱ እግዚአብሔር ወአሐቲ ሃይማኖት ወአሐቲ ጥምቀት — በአንድ ተስፋ እንደተጠራችሁ እንደ አካልና እንደ መንፈስ አለ አንድ ጌታ፥ አንዲት ሃይማኖት፥ አንዲት ጥምቀት»  (ኤፌ. 4፥4-6)። በዚህ የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ አስተምህሮ መሠረት ጥምቀተ ክርስትና አንድ ጊዜ ብቻ ይፈጸማል እንጅ አይደገምም፤ ጥምቀት አንዲት ናትና። በአንዲት ጥምቀት እናምናለን ተብሎ የተጻፈውም ስለዚህ ነው። ሃይማኖትን መለወጥ ጥምቀትን ማርከስ ለዘለዓለም ከእግዚአብሔር የሚለይ ክፉ በደልና ክሕደት ነው።

በእግዚአብሔር አምኖ በስሙ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ሥልጣነ ክህነት ባለው ካህን እጅ መጠመቅ የመንግሥተ ሰማያት በር መግቢያ ቁልፍ መያዝ፥ የዘለዓለም ሕይወት ማግኘት ነው። ስለዚህም ነበር ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ልጅነትን የምታሰጥ፥ የኀጢአት ሥርየት ብቻ የምትሆን ጥምቀት እያጠመቀ ፍጹም ለሆነ መርገመ ኀጢአት ለሚወገድበት፥ የሥላሴ ልጅነት ለሚገኝበት ጥምቀት ሲናገር፦ «ንስሐ ግቡ፤ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና» ብሎ ነበረ (ማቴ. 3፥4)። ይህም ማለት መንግሥተ ሰማያት በልጅነት በሃይማኖት ልትሰጥ ቀርባለችና እያለ ያስተማረውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትምህርቱ መጀመሪያ አድርጎታል። በዮሐንስ አድሮ የተናገረ እርሱ ስለሆነ ነው። (ማቴ. 4፥17)

ቅዱሳን ሐዋርያትም በበዓለ ጰራቅሊጦስ ሀብተ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ከአስተማሩ በኋላ ትምህርታቸውን የተቀበሉ ሕዝብ ምን እናድርግ ሲሏቸው፦ ንስሐ ግቡ ኀጢአታችሁ ይሰረይ ዘንድ ልጅነትን እንድታገኙ ከኀጢአት መርገም እንድትላቀቁ በኢየሱስ ክርስቶስ ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ትቀበላላችሁ፤ የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጅ ልጆቻችሁ ጌታ አምላካችን ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉት ሁሉ ነውና (ግብ. ሐዋ. 2፥37-40)።

የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን በመባል በሚታወቀው በበዓለ ጰራቅሊጦስ ቅዱሳን አበው ሐዋርያት በረድኤተ መንፈስ ቅዱስ ሲያስተምሩ በዚያች ቀን ብቻ ሦስት ሺህ ሰዎች አምነው ተጠምቀው ልጅነት ሀብተ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለዋል።

ጥንታዊት ሐዋርያዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በትምህርተ ሐዋርያት የተመሠረተች በመሆኗ የምንጊዜም የዕለት ተዕለት ተልዕኮዋ ወንጌል ማስተማር በመዓርገ ክህነት ማጥመቅ፥ ማቍረብ ነው። ቅድስት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳን አበው ሐዋርያት ትውፊትና ቀኖና፥ ሥርዐትና አስተምህሮ በመጠበቅ እስከ ሕልፈተ ዓለም ትኖራለች።

 

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሕረትና ይቅርታ በሁላችን ላይ ይሁን።

 

መጋቤ አእላፍ ኤፍሬም በየነ

የልሣነ ተዋሕዶ መጽሔት ዋና አዘጋጅ