“ከመንግስት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት የተሰጠ መግለጫ” በሚል ርዕስ በጥር ፳፰ ቀን ፳፻፲ወ፭ ዓ/ም የመንግስት ኮምዩኒኬሽን የሰጠውን መግለጫ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ህዝብ ግንኙነት መምሪያ የተሰጠ መግለጫ።
“ከመንግስት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት የተሰጠ መግለጫ” በሚል ርዕስ በጥር ፳፰ ቀን ፳፻፲ወ፭ ዓ/ም የመንግስት ኮምዩኒኬሽን የሰጠውን መግለጫ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ህዝብ ግንኙነት መምሪያ የተሰጠ መግለጫ።
በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በፍትሕ መንፈሳዊ እንዲሁም በሕገ ቤተክርስቲያን አንቀጽ ፲፱ ንኡስ አንቀጽ ፫ በተደነገገው መሠረት ጥር ፲፰ ቀን ፳፻፲ወ፭ ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ምልዓተ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ በተፈጠረው ወቅታዊ የሃይማኖት፣ የቀኖና እና የአስተዳደራዊ ጥሰቶችን አስመልክቶ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት ሕገ ወጥ ሲመተ ጵጵስና እና መፈንቅለ ሲኖዶስ ሙከራ በፈጸሙ ግለሰቦች ላይ ሃይማኖታዊ፤ ቀኖናዊ እና አስተዳደራዊ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ የቤተ ክርስቲያናችን የበላይ አካል በኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጡ ውሳኔዎች እና መልእክቶች ተከታታይ መድረኮች በማዘጋጀት ስለ ተፈጠረው የሃገራችን ሕግ እና የሕገ ቤተ ክርስቲያን ጥሰት በቂ ግንዛቤ ሕዝባችን እንዲያገኝ በተደጋጋሚ ከቅዱስ ሲኖዶስ እና ከብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት አማካኝነት መግለጫ እና ማሳሰቢያ ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል።
ይሁንና “በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከመንግስት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት የተሰጠ መግለጫ” በሚል ርእስ በጥር ፳፰ ቀን ፳፻፲፭ ዓ/ም የሰጠውን መግለጫ አስመልክቶ፤ መግለጫው ያስቀመጣቸው ነጥቦች የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ክብር፤ ታሪክ፤ እና እውነታ ቸል በማለት በጉዳዩ ላይ የተሟላ መረጃ የሌላቸው ወገኖች የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዙ የሚያስችል መግለጫ በመኾኑ በመግለጫው አንኳር ነጥቦች ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ተከታዩን ምላሽ ሰጥቷል።
፩. በመግለጫው የመጀመሪያ አንቀጽ ላይ “ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል የተፈጠረው መለያየት ሰላማዊ በሆነ መንገድ፣ በውስጣዊ አሠራር መፈታት እንዳለበት መንግሥት ያምናል” ያለውን በተመለከተ
፩.፩. እንደሚታወቅ በቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች መካከል የተፈጠረ መለያየት የለም። በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት በአባልነታቸው የሚታወቁ እና የቤተ ክርስቲያናችን አባቶች ተብለው እውቅና የሚሰጣቸው ነገር ግን አለመግባባት የፈጠሩ ብፁዐን አባቶች የሉም።
የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት የሰጠው መግለጫ፤ ብቸኛ ሕጋዊ ሰውነት ያላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመንፈስ ቅዱስ በታች የቤተ ክርስቲያናችን የበላይ አካል የኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ በቀኖናው መሠረት አውግዞ የለያቸውን ግለሰቦች አሁንም ሕጋዊ አካላት እንደኾኑ እና እውቅናም እንደሚሰጣቸው የሚያስረዳ መግለጫ ኾኖ ስላገኘነው ተገቢነት የሌለው ነው ብላ ቤተ ክርስቲያን ስለምታምን በመንግሥት ኮምዩኒኬሽን የተሰጠውን መግለጫ አትቀበለውም፤
፩.፪. ሰላማዊት የኾነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የመጨረሻው የበላይ አካል በኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ በውስጣዊ መንፈሳዊ እና አስተዳደራዊ አሠራሩ የሰጠውን የመጨረሻ ውሳኔ መንግሥት ያወጣው መግለጫ አሁንም የማይቀበለው መኾኑን የሚያመለክት ኾኖ አግኝተነዋል።
፩.፫. በመንግሥት መገናኛ ብዙኅን የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ድምጽ በማፈን አንድም መግለጫዎቿን እንዳይተላለፉ ከተደረገ በኋላ ይህንን የመንግሥት መግለጫ በእነዚሁ መገናኛ ብዙኅን እንዲተላለፍ በማድረግ ብዙኅኑ አድማጭና ተመልካች የተዛባ አረዳድ እንዲኖረው የሚያደርግ ይዘት ያለው መግለጫ መኾኑን ቤተ ክርስቲያን ትገነዘባለች፡፡
፪. በመግለጫው ሁለተኛ አንቀጽ ላይ “…የተቋማቱን አንድነት የሚፈታተኑ ችግሮች ከውስጥ ሲነሱ በውይይትና በውስጣዊ አሠራር እንዲፈቱ ድጋፍ ሲያደርግ ነበር” ያለውን በተመለከተ
፪.፩. በመግለጫው ከተጠቀሰው በተቃራኒ ቤተ ክርስቲያናችን ሕገ ወጥ ካለቻቸው ግለሰቦች እና ቡድኖች ጋር መንግሥት ጥምረት ፈጥሮ በመንቀሳቀስ ላይ መኾኑን በጥር ፳፯ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጠው መግለጫ ማሳወቁ የሚታወስ ሲኾን፤ መንግሥት ከዚህ ድርጊቱ አለመቆጠቡን የሚያሳይ ሆኖ አግኝተነዋል፤
፪.፪. መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ በቃሉ የሚናገር ኾኖ ሳለ በተግባር ግን ይህ መግለጫ እስከ ተሰጠበት ሰዓት ድረስ መንግሥት የሕገ ወጦቹን ስብስቦች ድጋፍ ከመስጠት ድርጊቱ አለመቆጠቡ እና በምእመናን ላይ ግድያ እስከ መፈጸም፤ የቤተ ክርስቲያናቱን ቅጽር ተዳፍሮ ለሕገ ወጥ ቡድኖቹ በመሳሪያ የታጀበ ድጋፍ በመስጠት የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ቁልፍ ሰብሮ በማስወረር ጭምር የሚፈጽመውን ፍጹም ያልተገባ እና ሕገ ወጥ የኾነ ድርጊት ለአድማጭ እና ለተመልካች ኹሉ ግልጽ ኾኖ ሳለ፤ መግለጫው ከዚህ ቀደም ክቡር ጠቅላይ ሚንስትራችን ከሰጡት እና ቅዱስ ሲኖዶስ መስመር በመስመር ነቅሶ ስህተቶቹን በመግለጽ እንዲታረም ካሳሰበው በተቃራኒ የክቡር ጠቅላይ ሚንስትራችን የተሳሳተ መግለጫ ቅጥያ ኾኖ አግኝተነዋል።
፫. በመግለጫው ፫ኛ አንቀጽ ላይ “የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ሁለቱን ወገኖች በማቀራረብ..” ሲል የገለጸውን በተመለከተ
፫.፩. ቅዱስ ሲኖዶስ ለክቡር ጠቅላይ ሚንስትራችን በሰጠው ምላሽ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው፤ መንግሥት ተወግዞ የተለየውን አካል ከቅዱስ ሲኖዶስ ጋር እኩያ እና ትይዩ አድርጎ መመልከት መቀጠሉን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አሁንም እየታዘበች ትገኛለች።
፫.፪. ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅጽሮቿ እየተደፈሩ እና ልዕልናዋ በመንግስት አጋዥነት እየተጣሰ ባለበት በዚህ ሰዓት መልስ ተሰጥቶበት የተዘጋውን የውስጥ አሠራር ጉዳይ ወደ ሽምግልና አውርዶ በማሳየት መግለጫውን ለሚሰሙ ኹሉ ግርታን የሚፈጥር ምሉዕ ምስል የማይሰጥና የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የተልዕኮ ምሰሶ በኾነው “ሽምግልና” በተባለ ክቡር ሃሳብ ላይ መዘባበት ኾኖ በማግኘታችን የተሰጠው መግለጫ ተገቢነት የሌለው ነው።
፬. በመግለጫው አራተኛ አንቀጽ ላይ ከተቀመጡ ሃሳቦች መሐል “…የጸጥታ አካላት የየአካባቢውን ሕዝብና የእምነት ተቋማት ሰላምና ጸጥታ ማስከበር ግዴታቸው ነው” እንዲሁም “… የሚዲያ አካላት ችግሩን የሚያባብሱ ነገሮችን ከማቅረብ መቆጠብ ይጠበቅባቸዋል” በማለት የገለጻቸውን ፍሬ ሐሳቦች በተመለከተ፤
፬.፩. በመግለጫው የተጠቀሰው ሀሳብ ልክነት ያለው ቢሆንም በተጨባጭ እየታየ ያለው ተግባር ግን ቅዱስ ሲኖዶስ በጥር ፳፯ ቀን ፳፻፲፭ ዓ/ም በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው መንግሥት ለሕጋዊቷ ቤተ ክርስቲያን የሕግ ጥበቃ እና ከለላ ከመስጠት ይልቅ በተቃራኒው ለሕገ ወጥ ቡድኖች በተግባር እየሰጠ ባለው ወገንተኝነት የምእመናንን ሕይወት እየነጠቀ እና የቤተ ክርስቲያናችንን ቅጽር በተደራጀ የጸጥታ ኃይል አጀብ እየደፈረ እና እያስደፈረ መኾኑን የካደ መግለጫ መሆኑን ቤተ ክርስቲያን በፍጹም ሐሳቧ ትረዳለች።
፬.፪. የመንግሥት መገናኛ ብዙኅን የቤተ ክርስቲያኒቱን የበላይ አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ የሚሰጣቸውን መግለጫዎች እንዳይዘግቡ በተግባር እቀባ ያደረገው መንግሥታችን ሕሊናዊ እና ሕጋዊ ተግባራቸውን እየፈጸሙ በሚገኙ የሚዲያ አካላት ላይ የማስፈራሪያ መግለጫ በመስጠት የቤተ ክርስቲያናችን ድምጽ ይበልጥኑ ለማፈን በመንቀሳቀስ ላይ መኾኑን በገሃድ ያመላከተ መግለጫ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ስለሆነም ፈጽሞ ተገቢነት የሌለው ተግባር ነው፡፡
፭. በመግለጫው ፭ኛ አንቀጽ ላይ “…ሀገር ለማፍረስ በተለያዩ መንገዶች ሞክረው ያልተሳካላቸው ኃይሎች፣ ችግሩ እንዲባባስና እንዳይፈታ ለማድረግ እየሠሩ መሆኑ ተደርሶበታል።” በማለት የተገለጸውን ፍሬ ሐሳብ በተመለከተ፡-
፭.፩. ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በማንኛውም ሁኔታ ሀገር የሚያፈርሱ ተግባራትን የምትጸየፍ፤ ዋነኛ ተልእኮዋም የሀገርን ሕልውና ማስቀጠል መኾኑን በተለያዩ የጦር ሜዳ ዐውዶች ላይ ታቦተ ሕጓን በማክበር ምእመናቶቿን ለትግል በመጥራት ጭምር የሀገርን ሕልውና ያስጠበቀች እና እያስጠበቀች ያለች መሆኗ የሚታወቅ ሲሆን መንግሥት በመግለጫው የገለጸው ዓይነት ተግባር ቢፈጸም የመጀመሪያ ተቃዋሚ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መሆኗን በድጋሚ ማስታወስ ትወዳለች። ለዚህም ማሳያዋ እያንዳንዱ እንቅስቃሴዋ ፍጹም ሰላማዊ እና የሕግ አግባብ እና መሠረትን ብቻ ተከትላ እየፈጸመች መገኘቷ ነው፡፡
፭.፪. ችግሩ እንዳይፈታና እንዲባባስ የሚፈልጉት ሀገር አፍራሽ ኃይሎች ሕገ ወጥ ቡድኖች መሆናቸውን መንግሥት ጠንቅቆ የሚያውቀውና ልዩ ድጋፍም የሚሰጠው መሆኑን ቤተ ክርስቲያን እያሳወቀች መንግሥትም ሕገ ወጦችን ከመደገፍ እና ከማገዝ ተግባሩ እንዲቆጠብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በድጋሚ ታሳስባለች።
፭.፫. እንደ መግለጫው ከሆነ ችግሩ የሚፈታው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሕልውናዋን፣ ሕጋዊነቷን፣ ተቋማዊ ነጻነቷን እና ከመንግሥት ልታገኝ የሚገባውን የሕግ ከለላ አጥታ ከሕገ ወጥ አካላት እኩል ስትታይ መሆኑን መግለጫው በግልጽ ቋንቋ ያስቀመጠ መሆኑን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በጽኑ የምታወግዘው እና የምትቃወመው መሆኑን ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡
፮. በመግለጫው የመጨረሻ አንቀጽ ላይ “..ችግሩን ለማባባስና በሕዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር፣ ሀገርን ወደፈተና ለማስገባት በሚጥሩ አካላት ላይ መንግሥት ሕግ የማስከበር ሥራውን እንደሚሠራ በዚሁ አጋጣሚ ያሳውቃል” በማለት ያስቀመጠውን በተመለከተ፡-
፮.፩. ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የበላይ አካል ከሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ አንስቶ እስከ ታችኛው የአስተዳደር መዋቅር አልፎም እስከ ተከታይ ምዕመኖቿ ድረስ የሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላም የሕዝቧ አንድነት እና የሕግ የበላይነት ጉዳይ ለድርድር እንደማታቀርብ በድጋሚ እያስታወስን ስልጣንን ተገን በማድረግ የቤተ ክርስቲያንችንን ሕጋዊ ጥያቄ በግድያ፤ በእስር፤ በማዋከብ እና በማስፈራራት ሊፈታ የማይችል ይልቁንም መንግሥት የተጣለበትን መንግሥታዊ ኃላፊነት ያለ አድሎ መፈጸም ሲችል ብቻ መሆኑን ቤተ ክርስቲያናችን ዳግም በጽኑ ቃል ለማሳሰብ ትወዳለች፡፡
በመጨረሻም መንግሥት ይህንን መግለጫ ሲያወጣ በጥር ፳፯ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በሻሸመኔ ከተማ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የተፈጸመውን ሕገ ወጥ፤ አስነዋሪ እና ጭካኔ የተሞላበት የአደባባይ ግድያ እና የሕዝብ ፍጅት ያልጠቀሰና ሐዘኑን እንኳን መግለጽ ያልቻለበትና ያላወገዘ መሆኑን ስንመለከት የመንግሥትን ግልጽ ሚና በቀላሉ ለመረዳት እንድንችል ያደርገናል።
ስለሆነም መንግሥት ሕገ ወጥ አካላትን ድጋፍ ከመስጠት እና የእነርሱ ልሳን ሆኖ በመቅረብ የቤተ ክርስቲያንን ክብር እና ልእልና ከሚያንኳስስ ሕገ ወጥ ድርጊት እንዲታቀብ እያሳሰብን ሕገ ወጡ ስብስቦች እየፈጸሙ ላሉት ድርጊትም የሰጠውን ድጋፍ እና እገዛ በይፋ ቤተ ክርስቲያንን ይቅርታ በመጠየቅ እንዲያቆም እናሳስባለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!
ጥር ፳፱ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ