ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የተላለፈ መልእክት
የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት መልእክት በብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒውዮርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፤ እንዲሁም በብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የተላለፈ ሲሆን ፣ በመልእክቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በማያወቀውና ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ባልጠበቀ መንገድ በእነ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የተሰጠውን ሕገ ወጥ ሢመተ “ኤጲስ ቆጶሳት” በማስመልከት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ባስተላለፉት ጥሪ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ነገ ጉባኤ ረቡዕ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በሚደረግ ሥርዓተ ጸሎት የሚጀመር መሆኑ ተገልጽዋል፡፡
በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት የሚገኙ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ወደ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት እየገቡ እንደሚገኙ በመልእክቱ ተወስቷል፡፡ መንግሥት እንደተለመደው ለጉባኤው ጥበቃ እንዲያደርግ መልዕክት ያስተላለፉት ብፁዕነታቸው ፤ ምእመናን በያሉበት በጸሎት እንዲበረቱ ጠይቀዋል፡፡
አንዳንድ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ሀገር ውስጥ ለመግባት ከፍተኛ የአውሮፕላን ቲኬት ችግር እንደገጠማቸው ተረድተናል ያሉት ብፁዕነታቸው ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚበርባቸው መስመሮች ለብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ቅድሚያ እንዲሰጥ ትብብር ተጠይቋል፡፡ በርካታ አህጉረ ስብከት እና መንፈሳዊ ማኅበራት የተፈፀመውን የቀኖና ጥሰት አስመልክቶ ውግዘት እያስተላለፉና እንደማይቀበሉት እየገለፁ ይገኛሉ፡፡
©EOTC TV