ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የተላለፈ ወቅታዊ መልዕክት።
ጥንታዊት፣ ታሪካዊት፣ ብሔራዊትና ዓለም አቀፋዊት በሆነችው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥር ከሚገኙት ጥንታዊያን ገዳማት መካከል ዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም አንዱና ዋነኛው መሆኑ ይታወቃል።
ይህ ጥንታዊና ታሪካዊ ገዳም በርካታ ቅርሶችና መናንያን የሚገኙበት ገዳም ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት በተከሰተበት ዘረፋና ቃጠሎ ከባድ ጉዳቶችን ያስተናገደ መሆኑም ይታወሳል።
በዛሬው ዕለት ከሀገረ ስብከቱ በደረሰን መረጃ መሰረትም፦
1. የገዳሙ መጋቢ አባተክለማርያም ዐሥራት
2. የገዳሙ ጸሐፊ አባ ኪዳነ ማርያም ጥላሁን
3. የገዳሙ የመጽሐፍ መምህርና ቀዳሽ አባ ገ/ማርያም አበበ
4. በአመክሮ የሚኖሩ መናኝ ኃይለማርያም ወልደሰንበት
የካቲት 12 ቀን በታጣቂ ቡድኖች ከተወሰዱ በኋላ አራቱም በትላንትናው አለት የተገደሉ ሲሆን አባ ኪዳነማርያም ገ/ሰንበት የተባሉት አባት ቆስለው በገዳሙ እንደሚገኙ ታውቋል።
በአሁኑ ሰዓትም ታጣቂዎቹ ወደ ገዳሙ ለመግባት እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት መንገድ እንዳይኖርና መናንያኑና የገዳሙ ቅርስ አደጋ ላይ እንዳይወድቁ የፌዴራልና የክልሉ የጸጥታ አካላት ገዳማዊያኑንና ገዳሙን የመታደግ ሥራ እንዲሠሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከአደራ ጭምር መልዕክቷን ታስተላልፋለች።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት
የካቲት ፲፬ቀኝ ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ