ሚያዝያ ፱ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ዓ.ም
“””””””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
******
ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ዛሬ ሚያዝያ ፱ቀን ፳፻ ፲ወ፭ዓ.ም በጠቅላይ ቤተክህነት ጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ በተካሄደው የእንኳን አደረሰዎ መርሐ ግብር ላይ ያስተላለፉት አባታዊ መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።
*ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሀይማኖት፤
*ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤
*ክቡር ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን የጠቅላይ ቤተክህነት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ፤
*ክቡራን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያ ኃላፊዎችና የየድርጅቶቹ ኃላፊዎች፤
*ክቡር ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ ጸጋዬ የአዲስአበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤
*ክቡር ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጠቅላይ ጸሐፊ፤
*ክቡራን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች ፤
*ክቡራን የቤተክርስቲያናችን ማኅበራት አመራሮች፤
*ክቡራንና ክቡራት
ከሁሉ አስቀድሞ ቡራኬዎ ይድረስኝ እያልኩ የእንኳን አደረሰዎ መልዕክት እንዳቀርብ እንዲፈቀድልኝ በታላቅ ትህትና እጠይቃለሁ።
“በአማን ተንሥአ እግዚእነ፤ በእውነት ጌታ ተነስቷል”ሉቃ 24፥34
ከሁሉ አስቀድሞ አምላካችን እግዚአብሔር ባለፉት ወራት በሀገራችንም ሆነ በቤተክርስቲያናችን የተከሰተውን ፈተና አሳልፎ ማዕበሉን ገቶ ከዚህ ስላደረሰን ክብርና ምስጋና ለእርሱ ይሁን እያልሁ ቅዱስነትዎ በሆነው ሁሉ በሀገርም ሆነ በቤተክርስቲያን ላይ ለመጣው ፈተና ግንባር ቀደም የመከራው ተካፋይ መሆንዎ ቢታወቅም ልዑል እግዚአብሔር ፈቃዱ ሆኖ ኃዘንዎና ድካምዎን ተቀብሎ የሕማማቱን ወራት አሳልፎ ለበዓለ ትንሣኤው ስላደረሰዎ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ስም እንኳን አደረሰዎ እላለሁ።
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፤
ይህ ዕለት ቤተ ክርስቲያን ታላቁን የምሥራች ያበሰረችበት ኃዘንን ጨርሶ የሚያጠፋ የደስታ ስብከት በመላዕክት አንደበት የተሰበከበት ታላቅ ቀን ነው።ከመላእክት ጋር በዓል እያከበርን ከመላእክት ቃል ሦስተኛውን የደስታ ዜና “ለምንት ተኃሥሣሁ ለሕያው ምስለ ምውታን ተንሥአ ኢሀሎ ዝየሰ፤ሕያውን ከሙታን ጋር ስለምን ትፈልጉኛላችሁ ተነሥቷል በዚህ የለም”ሉቃ24፥5 ብለው አይሁድ የሚፈሩትን ፣ እኛ ግን ልንሰማው ስንጠባበቀው የነበረውን ታላቅ ደስታ የሰማንበት ቀን በመሆኑ ደስታችን ዕጥፍ ድርብ ነው።መላዕክት የነገሯቸው ሴቶች ሂደው ትንሣኤውን ካወሩላቸው በኋላ በደቀ መዛሙርቱ መካከል የነበረው ሹክሹክታ “በእውነት ጌታ ተነሥቷል”
የሚለው ነበር ።እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የትንሣኤው ምስክሮች የሚሆኑ ናቸውና በሦስት ነገር ትንሣኤውን አይተው እንዲያረጋግጡ አድርጓቸዋል ።
1. ከመላእክት አንደበት የመላእክትን ምስክርነት ሰምተው፤
2. ወደ መቃብሩ ገብተው መግነዙ ለብቻው ተጠቅሎ አንዱ በራስጌ አንዱ በግርጌ ወድቆ አይተው፤
3. በጉባኤ ተገኝተው አስቀድሞ በገሊላ ከዚያም በአግብኦተ ግብርና በጥብርያዶስ መነሳቱን ስለአዩ ነው።ከዚያም በተረዳ ነገር የሐዋርያትን ዐይን ዐይን አድርገን ለዘለዓለም “በእውነት ጌታ ተነሥቷል ” እያልን ስንመሰክር እንኖራለን ።
ይሁን እንጂ ትንሣኤውን እያከበርን ትንሣኤ ልቡና ያልተደረገለት ሰው እንዳይኖር ቅዱስነትዎ ጠንካራ ተግሣጽና ምዕዳን እንዲሰጡበት በታላቅ ትህትና ሳልጠቁም አላልፍም ። ዘመኑ የትንሣኤ ነው።ወቅቱ ከሲኦል ወደ ገነት የተሸጋገረበት የመሻገር ዘመን ነው።ትንሣኤ ልቡና ሳይኖር ትንሣኤን ማክበሩ፣ክፋት ወደ በጎነት ሳይሻገሩ”ክርስቶስ ፋሲካችን ” ነው ብሎ መናገር ምን ሊጠቅም ይችላል?
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን
ያለፈው ወቅት ቤተ ክርስቲያን ከውስጥና ከውጭ በሚፈልቁ ብዙና ብዙ የፈተና ማዕከል ተከባ የተጨነቀችበት ወቅት ነበር ።ቅዱስነትዎ ፈተናውን በትዕግሥትና በጥበብ እንዲሁም ቆራጥና በሳል አመራር በመስጠትዎ እስከ አሁን ጸንተን የቆምን ቢሆንም ነፋሱም መንፈሱን፣ጎርፉም መጉረፉን አቁሟል ማለት አይቻልም ።ስልቱን እየለዋወጠ የሚመጣብንን ብርቱ ፈተና በኅሊና ሞት ውስጥ ሆነን፣በሥጋ ምኞት መቃብር ውስጥ ተቀብረን ማሸነፍ እንችልምና ከወደቅንበት የራስን ጥቅም የማሳደድ አዚም ወጥተን የቤተ ክርስቲያንን ህልውና ሊያጸና የሚችለውን ሥራ እያስቀደምን ማገልገል የሁላችንም ውሳኔ መሆን አለበት።
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን
ቅዱስነትዎ ቤተ ክርስቲያን ዘመኑ ካመጣው ክፉ በሽታ ከዘረኝነት፣ከሙስናና ከሌላም መጥፎ ጠባይ ተላቃ በእውነተኛው የሐዋርያት መንገድ ስትሔድ ማየት እንደሚፈልጉ ከበዓለ ሢመትዎ ጀምሮ ባስተላለፏቸው ትምህርቶችዎና በዚህ ቅዱስ መንበር ከተቀመጡ በኋላ በሠሯቸው ሥራዎች ማረጋገጥ ይቻላል ።
ነገር ግን ምኞትዎ ተሳክቶ ሀሳብዎ ተፈጽሞ ለማለት ስንናፍቅ በዘመድና በገንዘብ ፍቅር የወደቀው፣ሹመትና ጥቅማ ጥቅም የሚያስጨንቀው ፣የፓለቲካና የጎሣን ጉዳይ ከሃይማኖታዊ ጉዳዮች በላይ አጀንዳ የሚያደርገው በመብዛቱ ቅዱስነትዎ የተመኙትን ያኽል ተሳክቷል ማለት አይቻልም። ጥሪያችን ከሐዋርያት ጋር የትንሣኤው ምስክሮች እንሆን ዘንድ ነው።የሐዋ.ሥራ 1፥22 ሆኖም የትንሣኤው ምስክሮች ለመሆን አስቀድመን ትንሣኤ ልቡና እንዲኖረን ለማድረግ ዛሬም ጸሎትዎ፣ጥበብና ማስተዋል ያልተለየው መመሪያዎ ወሳኝነት አለው።
ክርስቶስ ፋሲካችን ነው ስንል በትክክል በእርሱ ቁስል የተፈጠረውን በእርሱ ፋሲካነት የተሻገርን መሆናችንን አምነን በልማድና ለሰው ይምሰል ከመታየትና ከማስመሰል መራቅ አለብን።ነቅተውና ተግተው ይጠብቁ የነበሩ ደቀ መዛሙርቱ በትንሣኤው ሌሊት “ተነሥቷል “የሚለውን ዜና የሰሙት እንዲሁ በስንፍናና በግዴለሽነት እንዳልሆነ ሁላችንም የምናውቀው ሐቅ ነው። ከእነርሱ መካከል ሌሊቱን ሙሉ ግርማ ሌሊቱ ሳያስፈራራቸው የአይሁድ ጭካኔ ሳያስደነግጣቸው ወደ መቃብሩ ሲመላለሱ ያደሩ ነበሩ።አምላካችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ ምግብ ሳይቀምሱ የሚጠባበቁም ነበሩ። የትንሣኤውን ብርሃን ማየት”ተነሥቷል በዚህ የለም”የሚለውን የምሥራች ሰምቶ መቃብሩ ባዶ መሆኑን አይቶ ለማመን እንደ መቃብር ያለ ታላቅ ምሥጢር የለም።ሰማያት ተከፍተው አምላካችን ክርስቶስ በአብ ቀኝ ተቀምጦ ከማየት በፊት መቃብር ተከፍቶ ሰበኑ ተጠቅልሎ ክርስቶስም በብርሃን ተከቦ ማየት ይቀድማል ።ነገር ግን ያለ ብርቱ ጥረት ሰማያዊ ተስፋ የሚገኝ ባለመሆኑ በዋዛና በፈዛዛ የኖርንባቸው ያለፉትን ዘመናት ትተን ሁላችንም ተግተንና ነቅተን ለሕዝባችን የምንነግረው የምሥራች የሞላበት ዘመን እንዲሰጠን የቅዱስነትዎን መመሪያ አክብረን መሥራት የውዴታ ግዴታችን መሆን አለበት።
ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን
እንደ ተቃዋሚዎችን ሩጫ ቢሆን እዚህ ቀን ላይ መድረስ ለኛ ከባድ የነበረ ቢሆንም በቅዱስነትዎ ጸሎትና ቡራኬ በእግዚአብሔር ቸርነት እዚህ ደርሰናልና ከዚህ በኋላም ቅድስት ሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላሟ ጸንቶ፣ አንድነቷ ተረጋግቶ፣ጥንታዊትና ሐዋርያዊት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን አንድ መንበር፣አንድ ሲኖዶስ፣አንድ ፓትርያርክ ያላት ፍጹም አንድነቷ ከሁሉ በላይ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ከአባቶቻችን እጅ እንደተቀበልን እኛም ለሚመጣው ትውልድ አውርሰን
እንድናልፍ አምላከ አበው እግዚአብሔር ይፍቀድልን እያልሁ በድጋሜ ቅዱስ አባታችን ለበዓለ ትንሣኤው እንኳን አደረሰዎ እላለሁ።
“የቅዱስነትዎ ቡራኬ አይለየኝ”
አባ አብርሃም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ሚያዝያ ፱ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ