“ካለፈው ዓመት ስህተት ወደ አዲሱ ዓመት እንዳይሸጋገር ማድረግ እና ለሁለንተናዊ ለውጥ ራስን ማዘጋጀት ይኖርብናል”። ብፁዕ አቡነ ሄኖክ ሊቀ ጳጳስ

“ካለፈው ዓመት ስህተት ወደ አዲሱ ዓመት እንዳይሸጋገር ማድረግ እና ለሁለንተናዊ ለውጥ ራስን ማዘጋጀት ይኖርብናል”።
ብፁዕ አቡነ ሄኖክ ሊቀ ጳጳስ

ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ” የዘመናት ባለቤት እግዚአ ሰማያት ወምድር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለ 2017 ዘመነ ማቴዎስ የምሕረት ዓመት በሰላምና በጤና አደረሰን አደረሳችሁ” በማለት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

በመልእክታቸውም:-
” አዲስ ዓመት፤ የዓመታት፣ የወራት፣የሳምንታት እና የቀናት ለውጥና መፈራረቅ ብቻ ሳይሆን ካለፈው ዓመት ስህተት ወደ አዲሱ ዓመት እንዳይሸጋገር ማድረግ እና ለሁለንተናዊ ለውጥ ራስን ማዘጋጀት እንዲሁም የለውጥን ሂደት ለመጀመር ቁርጠኛ መሆንን ይጨምራል።

ለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱስ ቅን ልቡና፣ ቅን ሕሊና እሰጣችኃለሁ በማለት የሚነግረን፤ ዛሬ ላይ እንደ ደንጊያ ጽኑ እና ጨካኝ የሆነው ልባችን ቤተ ክርስቲያንን እና ምእመናንን እየጎዳ ይገኛል። ቅን ልቡና እና የተሰበረ መንፈስ ጠፍቶ በጎቻችንን በምድራዊ ሀሳብ እና በቁሳዊ ተራ እይታ መመልከት ከጀመርን ሰንብተናል።

በተለይም በአባቶች ደረጃ ለተጠራንበት ተልዕኮ መሥራት ካቆምን፣ ልጆቻችንን አስጨናቂ አገዛዝ ከጫንባቸው እና የምንመራቸው ልጆቻችን በምንከተለው ኃላ ቀር የመሪነት ዘይቤ ተሰላችተው ተስፋ ከቆረጡ ቆይተዋል። ለዚህ ድካማችን መፍትሔውም የድንጋዩን ልብ ከውስጣችን አውጥተን የሥጋን ልብ ለማግኘት መሥራት እንጂ ለዘመናት በኖረ መቋጠሪያ በሌለው ችግሮች ውስጥ ሆነን በኛ ድክመት የፈታነውን ሕዝብ ልዩ ልዩ እንቆቅልሽ እየፈጠርን ግራ ማጋባት ሊጠቅመው አይችልም።

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን
ምእመናንና ምእመናት:-

አዲሱን ዓመት ስንቀበል በአሮጌው ዓመት የነበሩ የክፋት ሥራዎቻችን፣ የልዩነት መንገዶቻችን እና የጥፋት ዕቅዶቻችን በአዲሱ መንፈስ የሚሻሩበት፤ ከጨለማው አመለካከታችን ወጥተን የብርሃን መንገድን ልንከተል፤ ያለፈውን የጥፋት ሥራ ያበዛንበትን ዓመት በአዲሱ ዓመት በንስሐ ታጥበን ለእውነት ልንሰራ ይገባናል።

በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን፥ አቁማዳው ይፈነዳል፥ የወይን ጠጁም ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል፤ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል፥ ሁለቱም ይጠባበቃሉ። እንዲል መጽሐፍ ቅዱስ በክፋት ባረጀው ሰውነታችን አዲስ ዘመንን መጨመር ከኃጢአት ላይ ኃጢአትን መጨመር እና የኃጢአት ክምርን ማብዛት ስለሚሆን ምን ጊዜም አዲስ ዓመትን ስንቀበል በንስሐ እና በጎ ተግባርን በማብዛት ሊሆን ግድ ይለናል።

አዲሱን ዓመት ስንቀበል፤ ራሳችንን ለለውጥ በማዘጋጀት፣ ሰላምን በመስበክ፣ ክርስቲያናዊ ተግባራትን በማብዛት፣የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት ሊሆን እንደሚገባ እያሳሰብን፤አዲሱ ዓመት የፍቅር፣የሰላም፣የአንድነት እና የስምምነት እንዲሆን እንመኛለን ፤በማለት አስተላልፈዋል።

+ አባ ሄኖክ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ጳጉሜን ፭ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ