መስከረም ፳፰ ቀን ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም
“”””””””””””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
=============

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተዳደር ጉባኤ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚስተዋለውን የግብረ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እንዲሁም እሱን ተከትሎ በጠቅላይ ቤተክህነት የሚታዩ ክፍተቶችን በመመርመር የውሳኔ ሐሳብ ጭምር እንዲያቀርብ የተቋቋመው ኮሚቴ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት አስተዳደር ጉባኤ እስካሁን ያከናወናቸውንና ወደፊት የሚያከናውናቸውን ተግባራት በተመለከተ ሪፖርት አቅርቧል።

ጉባኤውም በቀረበለት ሪፖርት ዙሪያ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ በቀጣይ ኮሚቴው በትኩረት ሊሰራባቸው በሚገቡ ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራ መመሪያ ሰጥቷል።በተለይም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ምርመራን ተከትሎ ሀገረ ስብከቱን ለመገንጠልና የቤተክርስቲያን አካላት የሆኑ ምዕመናን ሊያጣሩን አይገባም የሚለው ሀሳብ ቤተክርስቲያንን የሚከፋፍል ተግባር በመሆኑ ጉባኤው በጽኑ አውግዞታል።

አጣሪ ኮሚቴው አስተዳደር ጉባኤው በሰጠው አቅጣጫ መሰረት ቤተክርስቲያንን ወደ ክብሯ ለመመለስ በሚያስችል መልኩ ተቋምን መሰረት በማድረግ ብቻ ቤተክርስቲያንን ሊታደግና ለውጥ ሊያመጣ በሚችል አግባብ ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጦል መመሪያ በመስጠት የሚከተለውን ውሳኔ አስተላልፏል።

የአስተዳደር ጉባኤው ፍላጎትም ሆነ የአጣሪ ልዑኩ ተልዕኮ በተለያዩ ሚዲያዎች የጠፋውን የቤተ ክርስቲያንን ክብር በማስመለስ ቤተ ክርስቲያናችንን ወደጥንተ ክብሯ መመለስ በመሆኑ፡-
፩. አሁን ያለንበት ወቅት 43ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የሚካሔድበት ወቅት በመሆኑና ጠቅላይ ጽ/ቤቱም ይህ ታሪካዊ ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ እየሠራ የሚገኝ በመሆኑ የጠቅላይ ጽ/ቤቱን እና የቤተ ክርስቲያናችንን ሥራ የሚያደናቅፍ በሀ/ስብከቱ እና በአንዳንድ አድባራትና ገዳማት ኢ-መደበኛ የሆነ ሰላምን የሚያደፈርስ ሁከትን የሚያስከትል ምንም ዓይነት ስብሰባ እንዳይካሔድ ለሀ/ስብከቱ መመሪያ እንዲተላለፍ ሆኖ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ለማካሔድ በዝግጅት ላይ መሆኑን በመገንዘብ ጉዳዩን በመከታትል እርምት እንዲያደርጉና የሕግ ከለላ እንዲሰጡ በደብዳቤ እንዲገለጽ ይደረግ፤

፪.ቅዱስ ሲኖዶስ ከማጣራት ሒደቱ ተነስቶ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ከመሬት ኪራይ እንዲሁም ተመሳሳይ ከሆኑ የቋሚ ንብረቶች ጋር ተያይዞ የሚደረጉ ውሎች እንዳይፈጸሙ ለሀ/ስብከቱ ጥብቅ መመሪያ በጽሑፍ እንዲተላለፍ ይደረግ፤

፫. በጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባኤ በሀ/ስብከቱ የተፈናቀሉ አገልጋዮችን እንዲያስመልስ ከተሰየመው ኮሚቴ ጋር በመነጋገር የተፈናቀሉ ሠራተኞችን ከመመለስ ውጪ በዚህ ሰበብ የሚደረጉ ቅጥሮችና ዝውውሮች ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑ ታውቆ ምንም ዓይነት ቅጥርና ዝውውር እንዳይፈጸም ለሀ/ስብከቱ ጥብቅ መመሪያ በጽሑፍ እንዲተላለፍ ይደረግ፤

፬. የማጣራት ሒደቱን ተከትሎ ሀ/ስብከቱ ጉዳዩን ለማድበስበስና የተለየ ስያሜ ለመስጠት ከሀ/ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች ጀምሮ የአንዳንድ አድባራትና የገዳማት አስተዳዳሪዎችን፣ጸሐፊዎችን፤ ሒሳብ ሹሞችንና ቁጥጥሮችን በመሰብሰብ የሚደረገው የአድማ ስብሰባ የቤተ ክርስቲያንን ክብር ዝቅ የሚያደርግና ለችግሩ መፍትሔ የማይሆን ከመሆኑም በላይ በሁሉም የቤተ ክርስቲየናችን ሕጎችና ደንቦች አድማ ማድረግ የተከለከለ መሆኑ ታውቆ ሀ/ስብከቱ ከዚህ ድርጊቱ እንዲቆጠብ መመሪያ እንዲተላለፍ እንዲሁም የሚመለከተው የመንግሥት የጸጥታ አካል ይህን የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ህገወጥ ድርጊትን በተመለከተ ድርጊቱ ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ እውቅና ውጭ መሆኑን ተገንዝቦ አስፈላጊውን የሕግ ማስከበር ሥራ እንዲሠራ በደብዳቤ እንዲገለጽ ይደረግ፤

፭..አጣሪ ኮሚቴው አስተዳደር ጉባኤው በሰጠው አቅጣጫ መሠረት ቤተ ክርስቲያንን ወደ ክብሯ ለመመለስ በሚያስችል መልኩ ተቋምን መሠረት በማድረግ ብቻ ቤተ ክርስቲያንን ሊታደግና ለውጥ ሊያመጣ በሚችል አግባብ ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ይደረግ በማለት ወስኖ የዕለቱ ስብሰባ በብፁዕነታቸው ጸሎት ተጠናቋል፡፡