ወቅታዊ መልዕክት ለምዕመናን
የደብረ ኤልያስ ብሔረ ብፁዓን መልክዓ ሥላሴ አንድነት ገዳምን በተመለከተ በበርካታ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችና የመገናኛ አውታሮች ልዩ ልዩ ዘገባዎች እየተላለፉ ይገኛሉ።
ይህን ተከትሎም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ገዳማት አስተዳደር መምሪያ ከሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት ጋር በመገናኘት ተፈጸመ የተባለውን ችግር በተመለከተ በዝርዝር የማጣራት ሥራ እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤትም በማዕከል ደረጃ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ላይ ይገኛል።
ስለሆነም ዝርዝር ሁኔታው በሚገባ ተጣርቶ የተደረሰበት የማጣራት ውጤት እውነታውን በሚገባ በሚያሳይ መልኩ በቤተክርስቲያናችን ማዕከላዊ አስተዳደር የሚገለጽ ይሆናል።
በሌላ በኩል በአርሲ ሀገረ ስብከት በጢዮ ወረዳ በጨፌ ሚሶማ ቀበሌ ገበሬ ማኀበር በዴራ አማኑኤል አጥቢያ ቤተክርስቲያን ግንቦት ፳ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም ምሽት ላይ በኦርቶዶክሳውያን ላይ ደረሰ ተብሎ በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች የተገለጸውን ጥቃት በተመለከተ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የተሰማትን ጥልቅ ሐዘን እየገለጸች በሀገረ ስብከቱ በኩል ተጣርቶ በሚቀርቀው መረጃ መሰረት ጉዳዩን በህግ አግባብ የምትከታተለው መሆኑን ትገልጻለች። ልዑል እግዚአብሔር የሟች ወገኖቻችንን ነፍስ በአብርሃም፣በይስሐቅና በያዕቆብ ዘንድ እንዲያኖርልንም ቅድስት ቤተክርስቲያናችን የዘወትር ጸሎቷ ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
ግንቦት ፳፬ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም