ሐምሌ ፲፰ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ/ም
===================
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
“””””””””””””””””””””””
ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሐምሌ ፲፰ ቀን ፳፻፲ወ፮ ዓ/ም በሁለተኛው የአኅጉረ ስብከት ሰንበት ት/ቤቶች መምህራን የአሠልጣኞች ሥልጠና ማጠቃለያ መድረክ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት “ሰልጣኝ መምህራን አሁን የተፈጠረውን ትውልድና ያለንበትን ተጨባጭ ሁኔታ ታሳቢ አድርጋችሁ እንዲሁም ራሳችሁን መርምራችሁ ታዳጊዎችንና ወጣቶቹን ታሳቢ ያደረገ ሥራ መሥራት ይኖርባችኋል፤” ብለዋል።
አያይዘውም “እናንተ የተጠራችሁበት ዋና ዓላማ ቤተ ክርስቲያንን እንድትጠብቁ ነው። ለዚህም ንቁ መሆን፣ በሃይማኖት መጽናት፣ መጠንከርና በፍቅር መኖር መሰረታዊ ጉዳዮች መሆናቸውን ተረድታችሁ በፍቅር በአንድነት መንቀሳቀስ ይኖርባችኋል።” ያሉት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ታዳጊ ወጣቶቹ በአቋማቸውና በኦርቶዶክሳዊ ሃይማኖታቸው ጸንተውና በምግባር ታንጸው እንዲኖሩ ማድረግ ይቻል ዘንድ ቤተክርስቲያን ያደረገችላችሁን ጥሪ ተቀብላችሁ መገኘታቾሁ መታደል ነው፤ ብለዋል።
ባለፉት ቀናት የተሰጣችሁ ሥልጠና መልካም እና ውጤታማ መሆኑን በየ ጊዜው ከሚደረግልን ሪፖርት ተረድተናል ያሉት ብፁእነታቸው አሰልጣኞቻችሁም አይናማና የታወቁ በመሆናቸው አጥጋቢ ሥልጠና እንዳገኛችሁ እንረዳለን ካሉ በኋላ ያገኛችሁትን ሥልጠና ተጠንቶ ከቀረበው የመማሪያ መጻሕፍት ጋር በማጣጣምና በማዋሃድ ለሕጻናቱና ለታዳጊዎቹ በቂ ትምህርት በመስጠት በሃይማኖትና በምግባር የታነጸ ትውልድ ማፍራት የሚቻልበትን ሥራ እንደምትሠሩ ጥርጥር የለንም ብለዋል።
በመጨረሻም ሰልጣኝ መምህራኑ የየመጡበትን አህጉረ ስብከት በመወከል በርካታ ጥያቄዎችን አንስተው ብፁዕ አቡነ አብርሃም ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተውበታል።