ሰኔ ፳፬ ቀን ፳፻፲ወ፮ ዓ/ም አዲስ አበባ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ “በወንጌል ተልእኮ ትውልድን መታደግ” በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው ዓመታዊ የስብከተ ወንጌል ቀን በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽርሐ-ተዋሕዶ አዳራሽ በድምቀት እየተከበረ ነው።

መርሐ-ግብሩ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአከኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ጸሎት፣ ቡራኬ ቃለ ምእዳንና አባታዊ የሥራ መመሪያ ጀምሯል። ቅዱስነታቸው ስብከተ ወንጌል የቤተ ክርስቲያን መሰረትና አምድ መሆኑን አስረድተው የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የወንጌል ማዕከል የሆነው ሰላም ላይ አበክረው እንዲሠሩ፣ እንዲያስተምሩ “አእምሮአችንን የሰላም ማዕከል እናድርገው” ማለት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በዕለቱ አባታዊ መልእክታቸውን ያስተላለፉት ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የባሕር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ስብከተ ወንጌል የቤተ ክርስቲያናችን ዋና ተልእኮ በመሆኑ ይህንን ተልእኮ ያለድካም በመወጣት ሁሉም የቤተ ክርስቲያናችን አገልጋይ የየድርሻውን እንዲወጣ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የመምሪያው የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ እና የመምሪያው ዋና ኃላፊ መ/ሰ ቆሞስ አባ ቃለ ጽድቅ ሙሉጌታ (ዶ/ር) ይህንን ጉባኤ በማዘጋጀት ላደረጉት ከፍተኛ ጥረት ከቅዱስነታቸው እና ከብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ ምሥጋና ቀርቦላቸዋል። በጉባኤው ስብከተ ወንጌል ላይ ያተኮሩ ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው የተያዘው መርሐግብር ያሳያል።

በጉባኤው ከቅዱስነታቸው እና ከብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ በተጨማሪ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ።የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያና የድርጅት ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎች፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ሰባክያነ ወንጌል ተገኝተዋል።