ጳጉሜ 3/2016 ዓ.ም

“ሩፋኤል ግሩም በመንፈስ ቅዱስ ኅቱም
መዓዛ ቅዳሴከ ጥዑም ከመ ጽጌ ገዳም
ነዓ ነዓ ማዕከሌነ ቁም
በበዓልከ ባርከነ ዮም።

ዚቅ ዘበዓለ ሩፋኤል ዘወርሐ ጳጉሜን

በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በመንበረ ጵጵስና ወናጎ ወረዳ ቤተክህነት ሥር በምትገኘው በዲላ ዋለሜ ሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን የመልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል በዓለ ንግሥ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራአስኪያጅ መልአከ ሕይወት ቀሲስ ብርሃኑ ክፍሌ የሀገረ ስብከቱ የሥራ ክፍል ኃላፊዎች የወረዳ ቤተክህነት ዋና ሥራአስኪያጅ ሊቀጠበብት መሠረት ይልማ የአድባራት አስተዳዳሪዎች የዲላ ምዕመናን በተገኘበት በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።

የሀገረ ስብከቱ ዋና ሕዝብ ግንኙነት ክፍል እንደገለጹት መርሐ ግብሩን መልአከ ኃይል ቀሲስ ጌታሁን ገሠሠ የሀገረ ስብከቱ የቁጥጥር፣ የእቅድና ልማት ክፍል ኃላፊ የመሩት ሲሆን የደብሩ ሰንበት ት/ቤት ያሬዳዊ ወረብ አቅርበዋል ብለዋል። የዕለቱን የወንጌል ትምህርት ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ሀብታሙ አበበ የሀገረ ስብከቱ ስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ ‹‹ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ›› (ጦቢት ፲፪፥፲፭)፡፡ በሚል ርዕስ ስለ ቅዱስ ሩፋኤል ክብር ጥበቃና አማላጅነት ከቅዱሳት መጻሕፍት በመጥቀስ በሰፊው አስተምረዋል።

የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራአስኪያጅ መልአከ ሕይወት ቀሲስ ብርሃኑ ክፍሌ ቅዳሴውን በመቀደስ እና ቃለ ምዕዳን ያስተላለፉ ሲሆን የእግዚአብሔር መላእክት ያለቸውን ክብር በመዝ 33:7 ያለውን በመግለጽ ምዕመናን ችግራቸውን ሁሉ ለቅዱስ ሩፋኤል ቢነግሩ መፍትሔ የሚገኙ መሆኑን ገልጸዋል። እንዲሁም አዲሱን ዓመት ለመቀበል ሁሉም ክፋትን ምቀኝነት መጥፎ ሁሉን ነገር ማሻገር እንደሌለበት ንሰሐ መግባት እንደሚያስፈልግ አስተምረዋል። በመጨረሻም ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ተሰጥቶ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል ብለዋል ።

መረጃው የሀገረ ስብከቱ ህዝብ ግንኙነት ነው።