ጥር ፳፫ ቀን ፳፻፲ወ፮ ዓ/ም አዲስ አበባ።
* * *
በትናንትናው ዕለት የእድሳት ሥራው ተጠናቆ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ተባርኮ መንፈሳዊ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ታለቁ ገዳም በዛሬው ዕለት ብፁዕ አቡነ ቶማስ የአዊ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት ታቦተ አቡነ ተክለሃይማኖት ዑደት በማድረግ በዓሉን ለማክበር የተሰበሰቡ ውሉደ ክህነትና ውሉደ ጥምቀትን በመባረክ በዓሉ ተከብሯል።
እንደ ትላንቱ ሁሉ በበዓሉ ላይ የክብር ጥሪ የተደረገላቸው የመንበረ ፖትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የመምሪያ ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎች፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ምእመናንና ምእመናት ተገኝተዋል።
ከዑደት በኋላም የገዳሙ ሊቃውንት፣ ማኅበረ ዲያቆናትና የምክኀ ደናግል ሰንበት ት/ቤት መዘምራን ወረብ ቀርቧል።
ዕለቱን የተመለከተ ትምህርትም የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የመጻሕፍተ ሐዲሳት መምህር በሆኑት መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ ተሰጥቷል።
በበዓሉ ላይ ለሕንጻ እድሳት ሥራው መከናወን ከፍተኛውን ሥራ ለሠሩ የእድሳት ኮሚቴ አባላትና በተለያዩ መንገዶች ለተራዱ አካላት የተለያዩ የምሥጋናና የማስታወሻ ስጦታዎች በገዳሙ ተበርክተዋል።