ጥቅምት 27/2017 ዓ.ም
+ + +
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በጌዴኦ ኮሬና ቡርጂ ሀገረ ስብከት በመንበረ ጵጵስናና ወናጎ ወረዳ ቤተክህነት በአንዲዳ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራአስኪያጅ መልአከ ሕይወት ቀሲስ ብርሃኑ ክፍሌና የሀገረ ስብከቱ የየክፍል ኃላፊዎች የመንበረ ጵጵስናና ወናጎ ወረዳ ቤተክህነት ዋና ፀሐፊ ሊቀ ህሩያን እሸቱ ዋለ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን የአካባቢው ምዕመናን የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች በተገኙበት በታላቅ መንፈሳዊ ክብር ተከበረ።

ከለሊት ጀምሮ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በቅዱስ ያሬድ የተደረሰውን ማኀሌት በመቆም መንፈሳዊ ሐሴት ወረቡን በወረብ ኪደኑ በሀገረ ስብከቱ ሥራአስኪያጅ መሪነት ከተደረሰ በኋላ ታቦቱ ከመውጣቱ በፊት የመጀመሪያው ዙር የዝማሬና የስብከተ ወንጌል አገልግሎት የተከናወነ ሲሆን በዲ/ን ሀብታሙ አየለ “ስለመዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ስለተሰጠ ኃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኳችሁ እጽፍላችኋለው ። “ይሁዳ 1፥3 በሚል ርዕስ ሰፊ ትምህርት ተሰጥቷል።

ታቦቱ ከመንበረ ክብሩ ወጥቶ በሆታ በእልልታና በዝማሬ ሦስት ጊዜ ዑደት ካደረገ በኋላ በንበት ት/ቤት ተማሪዎች ለዕለቱ የተዘጋጀው ወረብ አቅርበዋል ። መርኃ ግብሩን የሀገረ ስብከቱ የልማትና ዕቅድና ቁጥጥር ክፍል ኃላፊ መልአከ ኃይል ቀሲስ ጌታሁን ገሠሠ መርተውታል። በየዕለቱን ትምህርት የሰጡት የሀገረ ስብከቱ ሂሳብና የምግባረ ሰናይ ክፍል ኃላፊ መምህር በየነ “ወአድኅነኒ እስመ ይፈቅደኒ…. ወዶኛልና አዳነኝ” መዝ 17፥18 በሚል ርዕስ ከዘላለማዊ ሞት የሰው ልጅን በፍቅሩ ያዳነውን ቤዛ ስለሆነን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰፊው አስተምረዋል።

በመጨረሻም ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የሰጡት የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራአስኪያጅ መልአከ ሕይወት ቀሲስ ብርሃኑ ክፍሌ ሲሆን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የመዳን ሥራ ለሰው ልጅ የከፈለውን ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሞት ወደ ሕይወት ማውጣቱን ዛሬም እኛ ከክፋት ከተንኮል ከምቀኝነት ከአድርባይነት ወጥተን እንደ እግዚአብሔር ቃልና ሃሳብ መጓዝ አለብን በማለት በሰፊው ቃለ ምዕዳን አስተላልፈው ቡራኬ በመስጠት በዓለ ንግሱ ፍጻሜ አግኝቷል።