ሰኔ ፲፭ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም
“”””””””””””””””””””””””””
በኢ.ኦ.ተ.ቤ. የምሥራቅ አውስትራሊያ እና ኒውዚላንድ ሀገረ ስብከት በጦርነትና በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት ለደረሰባቸው አብያተ ክርስቲያናት ማቋቋሚያ የሚሆን የ 2,091,000.00(ሁለት ሚሊየን ዘጠና አንድ ሺ) እርዳታ አበረከተ።

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረው ጦርነት እና መፈናቀል ምክንያት እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው አብያተ ክርስቲያናት ለጉዳት በመዳረጋቸው እና አገልጋዮች ችግር ላይ በመውደቃቸው ምክንያት አፋጣኝ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን ለመሥራት ይቻል ዘንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለሁሉም አህጉረ ስብከት ባስተላለፈው ተቋማዊ ጥሪ መሠረት የምሥራቅ አውስትራሊያ እና ኒውዚላንድ ሀገረ ስብከት በሥሩ የሚገኙ 14 አብያተ ክርስቲያናትን በማስተባበር የ 2,090,000.00 (ሁለት ሚሊየን ዘጠና አንድ ሺ) ብር እርዳታ በቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ በተከፈተው የባንክ ሒሳብ ቀጥር ገቢ አድርገዋል።

ሀገረ ስብከቱን በመወከል ገንዘቡን ገቢ በማድረግ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ሪፖርት ያቀረቡት የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ መልአከ ሰላም ቀሲስ ፍቅር ኃይለሚካኤል ናቸው። ተወካዩ ይህንን በልግስና የተበረከተ ገንዘብ ገቢ ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት ከሆነ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የተከሰቱ ችግሮች ካስከተሏቸው ማኅበራዊ ምስቅልቅሎች ሳንወጣ ጦርነቱ በመከሰቱና አብያተ ክርስቲያት በመጎዳታቸው ምእመናንም ችግር ላይ በመውደቃቸው በሀገረ ስብከቱ የሚገኙ ምእመናን ከፍተኛ ሀዘን ተሰምቷቸዋል ብለዋል።

አያይዘውም ለዚህም ጉዳይ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ሲያቀርብ ለምላሹ በመረባረብ የተጠቀሰውን መጠን ገንዘብ በማሰባሰብ ገቢ አድርጓል ካሉ በኆላ በተጨማሪም ሀገረ ስብከቱ ቤተክርስቲያን በሚዲያው ዘርፍ የምትሰጠውን መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲያግዙ ለተለያዩ በውጪ ሀገሮች ለሚገኙ አህጉረ ስብከት የተላለፈውን ጥሪ መሠረት በማድረግ የተወሰኑ ለሚዲያ አገልግሎት የሚውሉ መሳሪያዎችን ለመግዛትና ለማበርከት የቅድመ ዝግጅት ሥራውን እንዲጠናቀቁ የሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ መልአከ ሰላም ቀሲስ ፍቅር ኃይለሚካኤል ከድርጅቱ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ከብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ጋር ባደረጉት ውይይትገልጸዋል።