ነሐሴ ፲፪ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
===================
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
“”””“””””””””””””””””””

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ በማዕከል ደረጃ የሚከናውኑ ተቋማዊ ሥራዎችን በማጠናከርና በማዘመን ውጤታማ የሕዝብ ግንኙነት ሥራን መሥራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በሰሜን አሜሪካ ኒዮወርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ተካሔደ።

የምክክር መድረኩ በማእከል ባለፉት አራት ወራት ሲካሔዱ የሰነበቱትን ስልጠናዎችና በስልጠናዎቹ ማጠቃላያ ላይ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን መሠረት በማድረግ የተካሔደ ሲሆን፤ መምሪያው በአገር ውስጥ በአህጉረ ስብከት ደረጃ ያካሔዳቸውን የሕዝብ ግንኙነት አደረጃጀትን የማስፋትና በዝርወት በሚገኙ አህጉረ ስብከት ላይም መዋቅራዊ ትስስርን ለመዘርጋትና ለማጠናከርን የሚያደርገውን ጥረት ውጤታማ የሚያደርግ ነው፡፡

በዚህም መሠረት መሰል አደረጃጀቶችን በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓና በደቡብ አፍሪካ በሚገኙ አህጉረ ስብከትና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ላይ በመዘርጋት የሕዝብ ግንኙነት እና የተግባቦት ሥራዎችን ሙያዊ ክህሎትን መሰረት ባደረገ ስልት መሥራትና ውጤት ማስመዝገብ ይቻል ዘንድ በውጭ በሚገኙ አህጉረ ስብከት ደረጃ መዋቅሮችን መክፈትና ያሉትን ማጠናከር ጠቃሚ መሆኑ ተጠቁሟል።

የውይይት መድረኩ ዋና አላማም በመረጃ ልውውጥ ዙሪያ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በመሙላት ተቋማዊና ወጥነት ያለው የመረጃ መለዋወጫ ሥርዓትን በመዘርጋት ተቋማዊ መረጃዎችን በመሰብሰብና በማሰራጨት ረገድ በዘርፉ የሚስተዋለውን ክፍተት መሙላት መሆኑን የኢ/ኦ/ተ/ቤ/የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ ሊ/ት እስክንድር ገብረክርስቶስ በውይይቱ ወቅት ገልጸዋል።
በሰሜን አሜሪካ ኒዩወርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት በተካሔደው የምክክር መድረክ ላይ የመምሪያውን ሥራ ለማዘመንና ለማጠናከር የሚያስችል ጥናት እንዲደረግ ስምምነት ላይ ተደርሷል።

ሀገረ ስብከቱም ጥናቱን መሠረት ያደረጉ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎችን ለመስጠትና ለመምሪያው ሥራ መሳካት የሚያስፈልጉ ዘመናዊ ግብዓቶችን ማሟላት የሚያስችሉ ጥረቶችን እንደሚደርግም የኒወርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስና የሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች አረጋግጠዋል።

ለአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መስፋፋትና መጠናከር መወያየት፣መረዳዳት፣ መደጋገፍ እንደሚገባና በዚህ መልኩ ተቋማዊ ትስስር መጀመሩ አስደሳች መሆኑንም የጉባኤው ተሳታፊዎች በአጽንኦት ገልጸዋል።

የሕዝብ ግንኙነት መምሪያም በመሰል አጀንዳዎችና በመምሪያው የሥራ አፈጻጸም ዙሪያ በሰሜን አሜሪካ በሚገኙ አህጉረ ስብከት፣ በአውሮፓና በደቡብ አፍሪካ ተከታታይ የውይይት መድረኮችን የሚያካሒድ መሆኑም ታውቋል።