የካቲት ፪/፳፻፲፰ ዓ/ም

የቤተ ክርስቲያን ነገዎችን የተሻለ ለማድረግ ሥልጠና አስፈላጊ ሲሉ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና የስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ገለጹ።

ብፁዕነታቸው ይሄንን ያሉት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ከጥር 25_ የካቲት 6/2018 ዓ/ም በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች በሀገረ አቀፍ ደረጃ እንዲሰጥ ባስተላላፈው መምሪያ መሠረት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ከአራዳ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት እየተሠጠ በሚገኘው የሥልጠና መርሐ ግብር ላይ ነው።

በሥልጠናው የመክፈቻ አባታዊ መምሪያና መልእክት ያስተላለፉት ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ ሥልጠናው በቤተ ክርስቲያን የሚኖረው ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ሥልጠና ሳይሠሩ ከትናትና ጋር ቆሞ ከመቅረትና ከመቆዘም የሚያድን የቤተ ክርስቲያን ነገዎችንም የተሻለ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ብፁዕነታቸው አክውም ዘመኑ ዋጅተን በሥልጠና ራሳችንን እያሻሻልን ማገልገል ካልቻልን የዘመን ተከታዮች እንጂ ቀዳሚ መሆን ታሪክ እንዳይሆንብን በጥንቀቄ መጓዝ አለብን ብለዋል።

በሥልጠናው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አመሰራረት ታሪክ፣ሰበካ ጉባኤ የተመሰረተበት ዓላማ፣የሚስተዋሉትን ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው፣የሪፖሪት አቀራረብና አዘገጃጀት አስመልክቶ መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ቃለ ጽድቅ ሙሉጌታ (ዶ/ር) ስልጠና ሰጥተዋል።

በመቀጠልም “የሚዲያ አጠቃቀም በመንፈሳዊ ሕይወት ያለው ፋይዳ” በሚለው ርእስ መ/ር ማርቆስ ሥልጠናውን ሰጥተዋል።

በተነሡ የተለያዩ መወያያ ነጥቦች ላይ ውይይትና አስተያያት እንዲሁም ጥያቄ በተሳታፊዎች የተነሱ ሲሆን ከመድረኩ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

ለጠቅላይ ቤተክህነት ልኡካን ከክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት የምስጋና ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።

የሰበካ ጉባኤ አሠራር ማጠናከርና ተደራሽነቱንጨማስፋት እንዲሁም ከዘመኑ ጋር ራሳችንን ማብቃት እንዳለብን መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አስገንዘበዋል።

በሥልጠናውና በምክክር መርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕነታቸውን ጨምሮ መልአከ ሰላም አባ ቃለ ጽድቅ ሙሉጌታ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደረጃ መምሪያ ሐላፊና የዕለቱ አሰልጣኝ፣ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ መምህር ማርቆስ ተበቃ በስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅና የዕለቱ አሠልጣኝ፣ መጋቤ ሠናያት የቻለው ለማ የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው ሌሎች የሥራ ሐላፊዎች ተገኝተዋል።