የካቲት ፲ ቀን ፳፻ ፲ወ፰ ዓ.ም
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
=============

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለዘመናት ከመንግሥትና ከበጎ አድራጊ ግለሰቦች ያገኘቻቸውን ቤቶች፣ ሕንፃዎችና ይዞታዎችን እያስተዳደረች የምትገኝ ቢሆንም በታሪክ አጋጣሚ በድርጅቱ ረጅም ዘመናት ያገለገሉ ካልሆኑ በቀር በቀላሉ ቤቶቹን፣ሕንፃዎቹን እና ይዞታዎችን ከእነ አድራሻቸው ለመረዳት አዳጋች ነበር።

ይህንን የተረዳው የድርጅቱ አስተዳደር ጉባኤ ከሦስት ወራት በፊት ሰባት አባላት ያሉት አጥኚ ኮሚቴ አቋቁሞ በመጀመሪያ በመልሶ ማልማት ምክንያት የፈረሱ ቤቶችን በየክፍለ ከተማው ምትክ ያገኙና ያለገኙ ካሳ የተከፈለላቸው ያልተከፈለላቸውን በመለየት እንዲጠና ያደረገ ሲሆን በመቀጠልም አሁን ያሉ ቤቶች፣ሕንፃዎችና ይዞታዎች በየክፍለከተማው መብት የተፈጠረላቸውንና ያልተፈጠረላቸውን በመለየት እንዲጠና ተደርጓል ።

ይህንኑ ጥናት የድርጅቱ ሥራ ኀላፊዎች ብቻ ሳይሆኑ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤትም የቤተክርስቲያኒቱን የመሬትና የቤት ሀብት በቀላሉ ማወቅ የሚችልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ሙሉ ጥናቱን በወረቀትና በፍላሽ ዲስክ የድርጅቱ የስድስት ወራት ሪፖርት በቀረበበት እለት ርክክብ ተደርጓል።

ሰነዱን ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የምስካየ ኅዙናን መድኀኔዓለም ገዳም የበላይ ኀላፊ ከሊቀ ስዩማን እስክንድር ገብረ ክርስቶስ የቤቶችና ሕንፃዎች አስተዳደርና ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅና የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ዋና ኀላፊ የተረከቡ ሲሆን የተደረገውን እልህ አስጨራሽ ጥናት የዳረጉ አካላትንና በጥናቱ ላይ ተያያዥ ሚና ያላቸውን ሁሉ አመሰግነዋል።