መስከረም ፲፯ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ዓ.ም
******
አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ
“”””””””””””””””””””
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ በታላቅ መንፈሳዊ ሥነሥርዓት ተከብሮ የሚውለው የመስቀል ደመራ በዓል ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ ተከብሮ መዋል ይቻል ዘንድ ፲፫ ንዑሳን ኮሚቴዎችን በማደራጀት ስኬታማ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ስታከናውን መሰንበቷ ይታወሳል።
በዚህም መሰረት በእግዚአብሔር ቸርነት መስከረም ፲፮ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ዓ.ም የተከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ፍፁም ሰላማዊ፣ደማቅናአስደሳች በሆነ መልኩ ተከብሮ ውሏል።በበዓል አከባበር ሥነሥርዓቱ ላይ ሕዝበክርስቲያኑ የቤተክርስቲያንን እና የአባቶቹን ድምጽ በመስማት ያሳየው ክርስቲያናዊ ጨዋነትን የተላበሰ፣ የበዓል አከባበር ሥነሥርዓት በእጅጉ የሚደነቅና ምስጋና ሊቸረው የሚገባ በመሆኑ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ምስጋናዋን ታቀርባለች።
በበዓሉ ላይ ልዩ ልዩ ያሬዳዊ ዝማሬዎችን በተጠና፣ባማረ፣በተዋበና ለእይታ በሚማርክ መልኩ በተፈቀደላቸው መርሐ ግብር መሰረት በማቅረብ በዓላችንን ከፍ አድርገው ያሳዩ ካህናት፣ወጣት የቤተክርስቲያናችን ልጆችና ማኅበራት የበርካታ ቀናት ጥናትና ዝግጅታችሁ ውጤት ማራኪ በሆነ መልኩ በመስቀል አደባባይ ቀርቦ የበዓላችን ፈርጥ ሆኖ ታይቷልና ቤተክርስቲያን በሠራችሁት ሥራ የተሰማትን ደስታ ትገልጻለች።ምስጋናዋንም ታቀርባለች።
በዓሉ ከመቸውም ጊዜ በላይ በአማረና በደመቀ መልኩ ተከብሮ መዋል እንዲችል ዘመናዊ መደረክ፣የድምጽ ማጉያ ከነ ሙሉ ግብዓቱ፣ሙሉ ወጪውን በመሸፈን ያቀረበልን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም የበዓላችን ድምቀትና ማማር አካል መሆኑ የሚያስመሰግነው ነው።
ለዚህም ከተማ አስተዳደሩ በተለይም ክብርት አንቲባ አዳነች አቤቤ የቤተክርስቲያንን ጥሪ በመቀበል ላደረጉልን ትብብር ቤተክርስቲያን ምስጋናዋን ከታላቅ አክብሮት ጋር ትገልጻለች።
በዓላችን ያለምንም የጸጥታ ችግር በአማረና በደመቀ መልኩ ተከብሮ መዋል እንዲችል ለበርካታ ቀናት የጸጥታ ሥራውን በመምራትና በማስከበር ሂደት ውስጥ ጉልህ ድርሻ የነበራችሁ የፌዴራል ፓሊስ፣የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ፣የአዲስ አበባ ከተማ ፓሊስ ኮሚሽን አመራርና አባላት የሰራችሁት ሥራ ውጤታማ፣ የሚያኮራና የሚያስመሰግን በመሆኑ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ልባዊ ምስጋናዋን ታቀርባለች።
በአጠቃላይ በዓላችን ያለምንም ችግር በተሳካና ባማረ መልኩ ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ድጋፍ ያደረጋችሁልን አካላት በሙሉ ልዑል እግዚአብሔር ድካምና አገልግሎታችሁን እንዲቆጥርና እንዲባርክ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የዘወትር ጸሎቷ መሆኑን ስትገልጽ በዓለ መስቀልና አዲሱ ዓመት የሰላም፣የፍቅር፣የአንድነት፣
የመተሳሰብ ዓመት እንዲሆንላችሁ በመጸለይ ነው።
መስከረም ፲፯ቀን ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት