ጥር 1 ቀን 2017ዓ.ም. ( አዲስ አበባ)
+ + +
በመርሐ-ግብሩ በርካታ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ክቡራን ምክትል ሥራ አስኪያጆች፣ ክቡራን የየመምሪያ ኀላፊዎች ክቡር የአዲስአበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ክቡራን የድርጅቶች ሥራ አስኪያጆችና የመንፈሳዊ ኮሌጆች ዲኖች የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ሠራተኞች ክቡራን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሠራተኞች ፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ክቡራን የአባት አርበኞች አባላት፣ ክቡራን የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የጋሞ ብሔረሰብ ዘማርያንና ክቡራን ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
መርሐ -ግብሩ በጸሎተ ወንጌል የተከፈተ ሲሆን የየካ ደብረ ሳህል ቅዱስ ሚካኤል ካህናትና ዲያቆናት ጸሎተ ወንጌል አድርሰዋል። ከጸሎተ ወንጌል በመቀጠል የአንጋፋው የቅድስት ሥላሴ ዩንቨርሲቲ ደቀመዛሙርት በጎል ሰከበ በአጽርቅት ተጠብለለ (በበረት ተኛ በጨርቅ ተጠቀለለ) የሚለው ያሬዳዊ ዜማ አቅርበዋል። በመቀጠልም የአዲስአበባ ሀገረ ስብከት የአድባራትና የገዳማት አስተዳዳሪዎች ተወካዮች የእንኳን አደረሰዎ መልእክት አስተላልፈዋል ። በመልእክታቸው እጅም ሳይነካው ድንጋይ ከተራራው ተፈንቅሎ ከብረትና ከሸክላ የሆነውን የምስሉን እግሮች ሲመታና ሲፈጭ አየህ።”— ዳንኤል 2፥34 የሚል የመጽሐፍ ቃል በማንሳት የእንኳን አደረሰዎ መልእክታቸውን የጀመሩ ሲሆን ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ በዐበይትና በንዑሳን በዓላት የሰጡትን መልእክትና ያደረጉትን ሐዋርያዊ ሥራዎች በዝርዝር አቅርበዋል።
ነገረ ልደቱን ስናከብር በመንፈሳዊ ሥራዎች ሊሆን እንደሚገባም አውስተዋል ። የአዲስአበባ ሀገረ ሰብከት የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች የቅዱስነታቸው መመሪያ በመቀበል የተጣለባቸውን አደራ እየተወጡ እንደሆነ በመግለጽ እና ወደፊትም የቅዱስነታቸውም መመሪያ ለመተግበር ዝግጁ መሆናቸው በማሳሰብ መልእክታቸውን አጠናቀዋል ። ከዚህ በመቀጠል በሰንበት ትምርህት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የማዕከላዊውያን የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት “እንዘ አምላክ ውእቱ እምሰማያት ወረደ ከመ ይቤዙ ዓለመ” አምላክ ሆኖ ሳለ ዓለም ይቤዥ ዘንድ ከሰማያት ወረደ የተሰኘውን ያሬዳዊ ዜማ አቅረበዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የጋሞ ብሔረሰብ ዘማርያን በአማርኛና በጋሞኛ ዝማሬ አቅርበዋል።
በመቀጠልም የደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም ፣ የደብረ ጽጌ ቅድስት ድንግል ማርያም ገዳም ፣ የእቲሳ ተክለሃይማኖት ገዳም ፣ የምስካየ ኅዙናን መድኀኔዓለም ገዳም ፣የመናገሻ አምባ መድኃኔዓለም ገዳም እና የዐባይ ባንክ አክስዮን ማኅበር እንኳን አደረሰዎ በማለት ጸበል ጸዲቅ በቅዱስነታቸው አስባርከዋል። መርሐግብሩ ሊቃውንቱ በቅኔ እንኳን አደረሰዎ በሚሉበት የቀጠለ ሲሆን ከማኅደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም የመጻሕፍት እና የቅኔ መምህር የሆኑት ሊቅ ጀምሮ ሌሎች ሊቃውንትም ቅኔ አቅርበዋል።
የመርሐ-ግብሩ መገባደጃ ላይ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራአስኪያጅ የባሕርዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን በመወከል ክቡር ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት በመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤትን የእንኳን አደረሰዎ መልእክት አስተላልፈዋል። የሰው ልጅ የክርስቶስን መምጣት እንዲጠባበቅ ያደረገው አንዱና ዋነኘው ምክንያት እጦት ነው። የሰው ልጅ በሠራው በደል ምክንያት ልጅነትን አጥቶ ስለነበረ ሐዲስ ልደት ማግኘት አስፈልጎታል። ለዚህም ምላሽ እንዲሆን በእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ቤዛነት ዳግም ልጅነትን አግኝቷል። የሰው ልጅ ደግም የወራሽነትን መብትን አግኝቷል። በልደተ ክርስቶስ ቀን ደስታና ሐዘን ታይተዋል። ደስታው የመላእክት ዝማሬ ሲሆን ሐዘኑ ደግሞ በሄሮድስ እኩይ ሐሳብ ምክንያት ብዙ ሕፃናች መሰዋታቸው ነው። ከዚህ የምናየው ክፉና በጎ በተሠሳሳይ ጊዜ ሊከሰቱ እንደሚችሉ ነው። ይህ ሁኔታ በዘመናችንም በቤተክርስቲያናችን ይገጥማታል ። ነገር ግን በቅዱስነትዎ በሳል የአመራር ጥበብ የሚመጡትን ተግዳሮቶች እንደ አስተማሪ እንዲሁም የሚመጡ መልካም ነገሮችን እንደ ገጸ በረከት በመጠቀም ስለሚሠሩ ሁሌም መልካም እንደሚሆን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት ያምናል። በተለይም በወጣቱ ላይ ቢሠራና መሪ እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ የምናደርገው ጥረት ቤተክርስቲያንን የሚያሻግር መሆኑን በመግለጽ የእንኳን አደረሰዎ መልእክታቸውን አጠናቀዋል።
ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የእንኳን አደረሰዎ መልዕክት በመቀጠል በበብፁዕ አቡነ ማርቆስ ጋባዥነት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ለታዳሚዎች ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥትዋል።
ቅዱስነታቸው በሰጡት አባታዊ መመሪያ ታዳሚዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ጀምረው በዓለ ልደትን ያከበርንበትን ሰላማዊ አገልግሎት በማድነቅ የክርስቶስ መወለድና ወደዚህ ምድር መምጣትን ዋነኛ ዓላማን አብራርተዋል። በሁለት ሰዎች ስህተት ምክንያት የዘመናት ውድቀት ተከስቷል። ዘመኑም ዓመተ ፍዳ ተብሏል ። ነገርግን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ዘመን ተቀይሮ ዓመተ ምህረት ተብሏል። ጥንትም ቢሆን ሰዎችን ሲፈጥር ባለ አእምሮ አድርጎ ነው ። ነገር ግን ካደረጉት የጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ ለውድቀት ተዳርገዋል። ባለ አእምሮ ሆነን ሳለን አልሠራንበትም እንስሳት ባለአእምሮ የአይደሉም ነገር ግን ተንሸራተው ካልሆነ በቀር እያዩ ገደል አይገቡም እኛ ግን ባለ አእምሮዎች ሆነን ተፈጥረን እያወቅን ወደ ገደል እንሮጣለን።
እግዚአብሔር አእምሮውን ይስጠን በማለት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተው የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል።