የካቲት ፳፬ ቀን ፳፻ ፲ወ ፭ ዓ.ም
“””””””””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
******
የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ፲ኛ ዓመት በዓሉ ሢመት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በታላቅ ሥነሥርዓት ተከብሮ ውሏል።በበዓሉ ላይ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ቴጉሃን ታጋይ ታደለ የጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያና የድርጅትኃላፊዎች፣የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ተገኝተዋል።

ቅዱስ ፓትርያርኩ በዚሁ ጊዜ ” ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው “(ዮሐ17፥11)የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል መነሻ በማድረግ አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል።

አያይዘውም መለያየት አንዱን ወገን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም በእኩል ይጎዳል ሲሉ ገልጸዋል።

በቤተክርስቲያን የሚፈጠር መለያየት ከሌላው ሁሉ በባሰ ሁኔታ የማኅበረሰብን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ሕይወት በእጅጉ እንደሚጎዳ ጠቅሰዋል።

እግዚአብሔር አምላክ ከምንም በላይ መለያየትን ይጠላል፤ እንዲህ ባይሆን ኖሮስ ለምእመናን አንድነት ሲል ሰው ሆኖ ደሙን ባላፈሰሰ ነበር ብለዋል።

ከዚህ አኳያ በኅብረትና በአንድነት መኖር ለፍጡራን የውዴታ ሳይሆን የግዴታ ሆኖ እንዲቀጥል የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ትልቁ የችግር መፍትሔ ትዕግሥት፣ ውይይትና መቻቻል እንጂ ግጭት አይደለም ሲሉም መክረዋል።

ቤተክርስቲያን ያጋጠማትን ችግር በቀላሉ ለመፍታት የወሰደችው እርምጃ በንስሐ፣ በሰላምና በውይይት መፍታት የሚያስገኘውን መንፈሳዊ ጥቅም በመረዳት እንጂ የተፈጸመው ሕገ ወጥ ድርጊት ቀላል ስለሆነ አይደለም ብለዋል።

በሐዋርያት እግር ተተክተን የምንገኘው ሁላችንም ሊቃነ ጳጳሳት በጎቹን ለመበታተንና አለያይተን ለማፋጀት ሳይሆን ለማሰባሰብና አንድ ለማድረግ እንደሆነ ልንዘነጋ አይገባም ሲሉ መክረዋል።

ይህንን የማናስከብር ከሆነ በዓለ ሢመትን ማክበር ሥልጣነ ክህነትም አለኝ ማለት ምን ፋይዳ አለው? ስለዚህ አሁንም ሰከን ብለን እናስብና ወደ ልባችን እንመለስ በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የተከሰተው ችግር ለጊዜው መልክ ቢይዝም ቀጣይ ሥራ እንዳለን ግን ከሁኔታው አይተናል፤ ጉዳዩን በጥልቀት አይተን ዘላቂ መፍትሔን ማበጀት አሁንም ከእኛ ይጠበቃል በማለትጠቅሰዋል።

የቤተክርስቲያንን አንድነትና ህልውና ከሚያስቀጥለው ሐዋርያዊ ተልእኮ ባሻገር የቤተክርስቲያንን የሥራ አፈጻጸም ከአባካኝነት፣ ከአድልዎ፣ ከዘረኝነትና ከፖለቲከኝነት ለማጽዳት በቁርጠኝነት መሥራት አለብን፤ እሰከመቼ በዚህ ስንታማ እንኖራለን ከእንግዲህ ወዲህ በቃ ማስተካከል አለብን ሲሉ መክረዋል።በመጨረሻም

“……የቤተክርስቲያንን አንድነትና ህልውና ከሚያስቀጥለው ሐዋርያዊ ተልእኮ ባሻገር የቤተ ክርስቲያንን የሥራ አፈጻጸም ከአባካኝነት፣ ከአድልዎ፣ ከዘረኝነትና ከፓለቲከኝነት ለማጽዳት በቁርጠኝነት መሥራት አለብን።እስከ መቼ በዚህ ስንታማ እንኖራለን፤ ከእንግዲህ ወዲህ በቃ፤ ማስተካከል አለብን፤
ማስተካከል አለብን፤ማስተካከል አለብን።ብለዋል።