መስከረም ፳፬ ቀን ፳፻ ፲ወ ፮ ዓ.ም
አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ
ዛሬ በቦሌና ለሚ ኩራ ክፍላተ ከተማ በተደረገ የ፳፻ ፲ወ፭ዓ.ም የሥራ አፈጻጸም ግምገማና የአዲሱ ዓመት ዕቅድ ዙሪያ በተደረገ ስብሰባ ላይ በክፍላተ ከተማው ሥር የሚሚገኙ አድባራትና ገዳማት በተለይም ውጤታማ የሥራ ክንውን ላደረጉት የሽልማት መርሐ ግብር ተከናውኗል።
በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል አዳራሽ ዛሬ በተከናወነው መርሐ ግብር ሊይም ብፁዕ አቡነ ሔኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ብፁዕ አቡነ እንጦንስ የምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተገኝተው በክፍለ ከተማው በተካሔደው መርሐ ግብር ላይ አባታዊ መልዕክት፣ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የሰጡ ሲሆን በሥራ አፈጻጸማቸው ውጤታማ ለሆኑ አድባራትና ገዳማት እንዲሁም ለክፍለ ከተማው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የተዘጋጀላቸውን ሽልማት አበርክተዋል።
በዚሁ መርሐ ግብር ላይም በበጀት ዓመቱ የክፍላተ ከተማው ቤ/ክህነት ጽ/ቤት ከመንግሥት አካላት ጋር ተቀራርቦ መሥራት በመቻሉ በሰላም፤በልማትና በመልካም አስተዳደር የሚታይ ጉልህ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉ በልዩ ልዩ አካላት ተገልጿል።
የክፍለከማው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ዓለምፀሐይ ሽፈራው በመርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ይህን በማረጋገጥ ለተገኘው ውጤት የመሪነት ሚናቸውን ለተወጡት መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነብርሃን ምስጋና አቅርበዋል።ሥራ አስፈጻሚዋ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ በመጠቀም የቤተ ክርስቲያን መብት እንዲከበር እና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን በማድረጋቸው ከብፁእ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ልዩ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በሁለቱም ክፍላተ ከተሞች በሚገኙ ገዳማትና አድባራት ሰላምና ልማት እንዲሰፍን ያደረጉ የክፍለከተማው ሠላምና ፀጥታ የሠራተኛ ራ ኃላፊዎችና የክፍለከተማው ፖሊሰም በዚሁ መርሐ ግብር ላይ በልዩ ሁኔታ ተሸልመዋል።
የክፍላተ ከተሞቹ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በ፳፻ ፲ወ፭ ዓ፡ም ካከናወናቸው ዋና ዋና የልማት ሥራዎች መካከልም የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ይዞታ መብት ማስከበር፡ የአዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት ምስረታ፥ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ማስገኘት፤ የክፍለከተማ ዋና ጽ/ቤት መስሪያ ከ፩ሺህ ፱፻ ካሬ ሜትር እና ፬ሺህ ካሬ ሜትር ለልማት የሚውል ቦታ ከመንግሥት ማግኘቱ ተጠቅሷል።
ከዚህ በተጨማሪ የጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎችን ማግኘቱንና ከ፳፻ ፲ወ፬ ዓ፡ም በጀት ዓመት የ፴፰ ሚልዮን ብር ብልጫ ያለው ፐርሰንት ከገዳማትና አድባራት መሰብሰቡ ተገልጿል።
ብፁእ አቡነ ሄኖክ በበዓሉ ላይ ለተገኙ እንግዶችና ውጤታማ ለሆኑ ገዳማትና አድባራት ሽልማት ከሰጡ በኋላ በሰጡት አባታዊ መመሪያ በ፳፻ ፲ወ፭ ዓ፡ም የታየው የሥራ መነሳሳትና ውጤት በ፳፻ ፲ወ፮ ዓ፡ም ተጠናክሮ እንዲቀጥል መመሪያ ሰጥተዋል።
በዚሁ ደማቅና በአርአያነቱ በሚደነቀው በመርሐ ግብር ላይ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎች ፣ በክፍለ ከተማው ሥር የሚገኙ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ፣ ካህናት ፣ ዲያቆናት ፣ ዘማርያን ፣ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪ ወጣቶች ተገኝተዋል።
መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነብርሃን የቦሌና ለሚኩራ ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የክፍላተ ከተማው አሰራር ዘመናዊነትን የሚከተል፣ውጤታማ ሥራ የሚከናወንበት፣የታቀደ የሚለካና ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ መሆን ይችል ዘንድ የመሪነት ድርሻቸውን በሚገባ የተወጡ መሆኑን በየ ዓመቱ የሚያካሒዱት የሥራ አፈጻጸም ግምገማና የወደፊት የትኩረት አቅጣጫዎች ጠቋሚ መርሐ ግብሮች በቂ ማሳያ ናቸው።መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነብርሃን ቀድሞ በነበሩበት ደብር ተቋማዊ፣ሕጋዊና ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ያስጠበቀ ውጤታማ ሥራ ያከናወኑ ብርቱ መሪ መሆናቸውም ይታወቃል።