ኅዳር ፲፰ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ዓ.ም.
“”””””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
==============

በዛሬው ዕለት የጠቅላይ ቤተክህነትና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስተዳደር ጉባኤ በጋራ ባደረጉት ስብሰባ በርካታ ጉዳዮች ተነስተው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።የውይይቱ ዋነኛ ማዕከልም በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እንዲመራበት የተደረገውን መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ያደረገና በተለይም ከመልካም አስተዳደር አንጻ የሚታዩ ክፍተቶችን በመፈተሽ በትብብርና በአንድነት የቤተክርስቲያንን ሥራ መሥራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያጠነጠነ ነበር።

በዚሁ ጉባኤ ላይም ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ” ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፥ በጨው እንደ ተቀመመ፥ በጸጋ ይሁን።”(ወደ ቆላስይስ ሰዎች 4:6)የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሀይለ ቃል መሰረት በማድረግ በሀገረ ስብከቱ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በውይይት፣በመግባባትና ተቋምን ማዕከል በማድረግ መፍታት የሚቻልበትን መንገድ ለመቀየስ ውይይቱ ማስፈለጉን ሲገልጹ የመድረኩ ዓላማም ለመተቻቸት፣ለመነቃቀፍና ለመወነጃጀል ሳይሆን ለአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን ሁለንተናዊ አገልግሎት መቀላጠፍ በጋራ ለመስራት መሆኑን ገልጸዋል።

በውይይቱ ማጠቃለያ ላይም ጉባኤው በጋራ የተስማማባቸው ነጥቦች ሕጎች፣ደንቦችና መመሪያዎች ተከብረው በጋራ የሚሰራበትን አቅጣጫ የተከተለ በመሆኑ ለመልካም አስተዳደር መስፈን በጋራ እንሰራለን የሚል መግባባት ላይ በመድረስ እንደተጠናቀቀ በስብሰባው ወቅት የተቀረጸ የቪዲዩ ማስረጃ ያረጋግጣል።

ይሁን እንጂ ሀቁ ይህ መሆኑ እየታወቀ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ የተዛባ መረጃ በማሰራጨት ሀቁን ለመደበቅ ከመጣሩም በላይ ቅዱስ ሲኖዶስ ሀገረ ስብከቱ እንዲመራበት ያወጣውን መመሪያ አወላግዶ በማቅረብ አንባቢያንን ለማደናገር ሲጥር በመታየቱ በሀገረ ስብከቱ ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ የተላለፈውን መረጃ ቃል በቃል በመፈተሽ እውነታውን እንደሚከተለው ለመግለጽ እንገደዳለን።

“የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ቅዱስ ሲኖዶስ ያወጣቸውን ደንቦች በመጣስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ውስጥ የሚፈጽማቸው ጣልቃ ገብነቶች ሊታረሙ እንደሚገባ ተገለጸ !”በሚል ርዕስ የገለጸው ፍጹም በጉባኤው ላይ ያልተባለ ከመሆኑም በላይ ሀገረ ስብከቱ ሕግ በቅዱስ ሲኖዶስ ወጥቶ ተሰጥቶት እያለ ሕግ፣ደንብና መመሪያን በመተላለፍ የሰራቸው ሥራዎች የተገለጹበት ነበር።

“በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለዘመናት የቆየውን ብልሹ አሰራር እና ሕገወጥ ተግባራት ለመቅረፍ በማቀድ ቅዱስ ሲኖዶስ ሀገረ ስብከቱ ራሱን ችሎ በአንድ ሊቀ ጳጳስ እንዲመራ ከማድረግ ጀምሮ ለሀገረ ስብከቱ መተዳደሪያ ደንብ በማዘጋጀት አሠራሩ ሕግን እና ሥርዓትን የተከተለ እንዲሆን ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ይታወቃል። “በማለት የገለጸውም የዛሬው ጉባኤ ከፍ ሲል የተገለጸው ሕግ ተከብሮ ባለመሰራቱ የተፈጸሙ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ የተዘጋጀ ከመሆኑ አንጻር ሲታይ ዘገባው ማደናገሪያና አጀንዳ ማስቀየሪያ ሆኖ እንዲያገለግል የተዘጋጀ መሆኑን ያረጋግጣል።

“ይህንን ተከትሎ ቅዱስ ሲኖዶስ ከጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ ብፁዕ አቡነ ሄኖክን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አድርጎ በመመደብ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍንና የሀገረ ስብከቱን አገልግሎት የተቃና ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ችግሮች ሙሉ በሙሉ ተቀርፈው ተስተካክሏል በማለት ለመናገር ባያስደፍርም ሀገረ ስብከቱ ዘርፈ ብዙ የለውጥ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል። ” በእርግጥም በሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች የተገለጸ ቢሆንም የጉባኤው አጀንዳ ሪፖርት ማድመጥ ባለመሆኑ በዋናው አጀንዳ ዙሪያ ትኩረት እንዲደረግ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አቅጣጫ ተሰጥቶበት ወደ አጀንዳው እንዲገባ ተደርጓል።

“በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አሉ የሚባሉ ችግሮችን በጋራ ለመፍታትና መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የጠቅላይ ቤተክህነትና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአስተዳደር ጉባኤ አባላት ባደረጉት የጋራ ጉባኤ አቅጣጫ ተቀምጧል። “ይህ ቃል እውነተኛና ትክክለኛ ሲሆን በጠቅላይ ቤተክህነት የሕዝብ ግንኙነት የፌስቡክ ገጽ ከተዘገበው ዘገባ ቃል በቃል የተወሰደ መሆኑን ለታዘበ ብቃትና ልምድ ያለው ዘጋቢ በሀገረ ስብከቱ የሌለ መሆኑንና ከሙያዊ አገልግሎት ይልቅ ሀሰትን በመዘገብ ከበሬታና ተወዳጅነትን ለማትረፍ ከሚጥር ጋዜጠኛ ተርታ የሚያስመድብ ነው።

“ሀገረ ስብከቱ ለጠቅላይ ቤተክህነት በይግባኝ የቀረቡ አቤቱታዎችና ለጉባኤው በአጀንዳነት የቀረቡት ሰነዶች በሸኚ ደብዳቤ እንዲደርሰው ተደርጎ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ እንደሚሰጥበት ብፁዕ አቡነ ሔኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በዚሁ ጉዳይ ላይ መግለጻቸውን ተገልጿል።”ይሔኛውም ሐቅ ነው በትክክልም ከጠቅላይ ቤተክህነት ሕዝብ ግንኙነት የፌስቡክ ገጽ ቃል በቃል የተቀዳ ነው ።

“በጉባኤው ላይ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ከሕግ ውጭ የሚፈጽማቸው ጣልቃ ገብነቶች እና መተዳደሪያ ደንቡን ለማስከበር በሚል ስም የሚደረጉ ሕገወጥ እንቅስቃሴዎች ሊቆሙ እንደሚገባ ተገልጿል።”በማለት የተገለጸው ፍጹም ሐሰትና የፈጠራ ወሬ መሆኑ በቪዲዩ የተቀረጸው የስብሰባው ውሎ በኢኦቲሲ ቲቪ ሲዘገብ ሕዝቡ ሀቁን የሚያውቀው ይሆናል።

“በጉባኤው ላይ መልእክት ያስተላለፉት ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ ከበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቀረቡት ክሶች ጥናት ያልተደረገባቸው ፣ ያልተጣሩ እና የአንድን ወገን አቤቱታ ብቻ በመያዝ የቀረበ በመሆኑ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ብፁዕነታቸው አቡነ ሄኖክ ላለፉት 30 እና 40 ዓመታት ተላልፎ የመጣ የውርስ ኃጢአት ላይ በአሁኑ ወቅት ያለው አስተዳደር ሊወቀስ እንደማይገባው እና ፖሊሲ በሌለበት ሁኔታ አንድን ወገን ኃጢአተኛ እና በደለኛ አድርጎ ማቅረብ አግባብ አለመሆኑን በጉባኤው ላይ አስገንዝበዋል ። “በሚል የቀረበው በእውነትም በብፁዕ አቡነ ሔኖክ የተገለጸ ሲሆን በወቅቱ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በሰጡት ቀጥተኛ ምላሽ ያደረ አጀንዳ የሚባለው ነገር ተቀባይነት የለውም እኛ እያነሳን ያለነው አሁን በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ የተካሔደውን ሕገ ወጥ ቅጥር፣ዝውውርና ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰውን የመልካም አስተዳደር እጦትን ነው።አስፈላጊ ከሆነ አንድ በአንድ ችግሮቹን እየጠቀስን መነጋገር እንችላለን።ሀገረ ስብከቱን ለማዳን በግልጽ ነው መነጋገር ያለብን በማለት የገለጹትን የሀገረ ስብከቱ ዘጋቢ ስለምን አልገለጸውም ቢባል ሀቁ እንዲነገር ካለመፈለግ ብቻ ሳይሆን ጥፋትን በመሸሸግ የሀገረ ስብከቱ ችግር ወደፊትም እንዲቀጥል ከመፈለግ የሚመነጭ ነው።ይህን በማድረግም ዘጋቢውን የእከክልኝ ልከክልህ መርህን ለማስቀጠል ያለመ ደካማ ጋዜጠኛ ያደርገዋል።

“ከሀገረ ስብከቱ የክፍል ኃላፊዎች ምደባ ጀምሮ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ሕግን የተላለፈ የሠራተኞች ምደባ እና ዝውውር በክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤቶችና በአጥቢያ አብያተክርስቲያናት ተመሳሳይ ጣልቃ ገብነት በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እየተፈጸመ እንደሚገኝ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ። “አልተባለም ይሔ ሀሳብ ሐሰትን ለማንገስ የሚደረግን ጥረት የሚያመለክት ሲሆን ከኃላፊነት ለመሸሽም ማስረጃዎች ይጠቁማሉ ይለናል በመሰረቱ ዛሬ በተደረገው ስብሰባ በጠቅላይ ቤተክህነቱ በኩል አሉ የሚባሉ ችግሮች በግልጽ እንዲቀርቡ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ሲጎተጎቱ የዋሉት የሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች አንዲት ነጥብ እንኳን ማስቆጠር ተስኗቸው ሲደናበሩ መዋላቸውን በቅርቡ ሙሉ የስብሰባው ዘገባ ሲለቀቅ አንባቢያችሁ አንቅሮ ይተፋችኋል።

“ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ በቀድሞ የሀገረ ስብከቱ ኃላፊዎች የተፈፀመው የትግራይ ተወላጅ ሊቃውንት እና አገልጋዮችን የማፈናቀል ተግባር በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ምላሽ አግኝቶ ወደ ሥራ ገበታቸው መመለሳቸው የተገለጸ ሲሆን በተለየ መልኩ እነዚሁ ወንድሞቻችን የሥራ ምደባ ሳይሆን የደረጃ ጥያቄ እንዳላቸው እና ይኸውም የሥራ ደረጃ ጥያቄያቸው በሂደት የሚፈታ ስለመሆኑ ነው የተጠቆመው።”የሚለውን በተመለከተ በማስረጃ ያልተመለሱ አገልጋዮች እንዳሉ ቀርቦ በጋራ ስምምነት የተደረሰበት መሆኑን ዘጋቢው በጉባኤው ላይ ከተገኙ የሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች ጠይቆ ቢረዳ መልካም ነበር ነገር ግን የምስል ዜናው በቅርቡ ሲለቀቅ የሚያስተዛዝበን ይሆናል።

“ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ የምንሰራው ሥራ መንፈሳዊ አገልግሎት እንደመሆኑ መጠን እውነትንና እውነተኛነትን ብቻ መሰረት ባደረገ አግባብ መከናወን እንዳለበት በጉባኤው የገለጹ ሲሆን ካህናትና ምዕመናንን ከሚያሳዝንና በቤተክርስቲያን ላይ አመኔታን ከሚያሳጣ ሥራ በመራቅ ሀቅን መሰረት በማድረግ ሊሰራ እንደሚገባ የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል።”ይሔኛውም ሀሳብ በትክክል በጉባኤው ላይ የተገለጸ ነው።ቃል በቃልም ከጠቅላይ ቤተክህነት ሕዝብ ግንኙነት ዘገባ የተወሰደ ሲሆን ሀሳቡ የሚያመለክተውም በመልካም አስተዳደር ችግር ውስጥ የተዘፈቀውን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን እንደሆነ ያልተረዳው ዘጋቢው ከላይ የተረከውን መሰረተቢስና ሐሰተኛ ዘገባ እንደሚንድበት አለመረዳቱ የሚያሳዝን ሲሆን ሐሰተኛ ዘገባ በመለጠፍ የመልካም አስተዳደርን ችግር መፍታት እንደማይቻልም የሚያረጋግጥ ሆኖ አጊንተነዋል።

ከሁሉ የሚገርመውና ዘገባው ሐሰተኛ መሆኑን የሚያረጋግጠውም ዘገባው በተለቀቀ በአርባ ደቂቃ ውስጥ ከሀገረ ስብከቱ የፌስቡክ ገጽ ላይ መነሳቱ ነው።