የአሶሳ እንዚ መካነ ገነት መድኃኔአለም ካቴዴራል የህንፃ ግንባታ ኮሚቴ የመንበረ ጵጵስና ገዳማትና አድባራት የማጠናቀቂያ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉለት ጠየቀ፤

ሀ/ስብከቱ የአሠሪ ኮሚቴውና የካቴዴራሉ ሰበካ ጉባኤ ያቀረበውን ጥያቄ መሠረት በማድረግ ከመንበረ ጵጵስና ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና የሰበካ ጉባኤ አባላት ጋር ውይይት አድርጓል።

ውይይቱን የመሩት የሀገረስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ፀሐይ ቆሞስ አባ ዘካርያስ ፀጋ እንደገለጹት የህንፃ ግንባታውን ምርቃት በተመለከተ የካቴዴራሉ ሰበካ ጉባኤ እና የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት ኃላፊነት ወስደው ዐብይ ኮሚቴ በማቋቋም ወደ ሥራ እንደሚገባ ገልጸው የመንበረ ጵጵስ ገዳማትና አድባራትን በመያዝ ካህናትን ሰብስቦ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ ገልጸው ግንዛቤ

የተፈጠረላቸውን ካህናት በማሠማራት የማጠናቀቂያ የገቢ ማሰባሰብ ሥራ በመሥራት እስከ መጋቢት 27 ቀን 2016 ዓ/ም ሥራው ተጠናቆ በዘመነ ትንሣኤ ለማስመረቅ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሀገረስብከቱ ዋና ፀሐፊ ሊቀልሳናት ትህትና አበበ በበኩላቸው የመንበረ ጵጵስና ገዳማትና አድባራት አጥቢያ አቢያተክርስቲያናት የሰበካ ጉባኤ ካህናትና ምዕመናን በህንፃ ግንባታው ማስፈጸሚያ የገቢ አሰባሰብ ንቅናቄ ሥራ ላይ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባቸው ተናግረው ይህም የቤተክርስቲያን አንድነት መገለጫ ነው ብለዋል። ምንግዜም ቢሆን የቤተክርስቲያን አንድነት በሥራ መገለጽ እንዳለበት በሰፊው ያብራሩት ዋና ፀሐፊው በየደረጃው ያለን የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ፍቅርን እና አንድነትን በመያዝ የትብብርን መንፈስ ማዳበር አለብን ብለዋል።

የአሶሳ እንዚ መካነ ገነት መድኃኔአለም ካቴዴራል ዋና አስተዳዳሪ ሊቀ-አዕላፍ አባ ገ/መስቀል ምንዳ እንደተናገሩት አሁን ሥራውን አጠናቆ ለማስመረቅ አራት ሚልዮን ብር እንደ ሚያስፈልግ ገልጸው ብሩን ለማሰባሰብ የመንበረ ጵጵስና ገዳማትና አድባራት የሚችሉትን ተከፋፍለው ቃል እንዲገቡ ካህናት ግንባር ቀደም ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ለማስቻል በሀ/ስብከቱ በኩል ጥሪ ተደርጎ ምክክር ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አስታውሰዋል።

የህንፃ ግንባታ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ አቶ ይሁን ጉዴታ እንደገለጹት ምዕመናን በዓይነት ድጋፍ እንዲያደርጉ በመድኃኔዓለም ስም ጠይቀው የሙሌት ሥራ ለመሥራት አሥር ቢያጆ ሀርድ ኮር ድንጋይ”፤ አምስት ቢያጆ አሸዋ፤ ሁለት መቶ ሃምሳ ኩንታል ስሚንቶ፤ የኳርቲዝ ቀለም በዋናነት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የመንበረ ጵጵስና ገዳማትና አድባራት አጥቢያ አቢያተክርስቲያናት አስተዳዳሪዎችና የሰበካ ጉባኤ አባላትም የሚችሉትን ሁሉ ዴጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

በቅርቡም የገቢ ማሰባሰብ ንቅናቄውን ለመጀመር ከካህናትና ከዲያቆናት ጋር ምክክር እንደሚደረግ ውሳኔ ላይ ተደርሷል።

ዘገባው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ሀገረ ስብከት ህዝብ ግንኙነት ክፍል ነው።
ኅዳር 08 ቀን 2016 ዓ/ም
አሶሳ፤