የኢሉ አባ ቦር ሀገረ ስብከት ሲሰጥ የነበረውን የአሰልጣኞች ስልጠና አጠናቀቀ

መስከረም 9/2016 ዓ. ም

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የ10 ዓመቱን ስልታዊ ዕቅድ አውጥታ ወደ ሥራ ገብታለች። በዚህ መሠረት የኢሉ አባ ቦር ሀገረ ስብከት የ10 ዓመቱን መሪ ዕቅድ እስከታችኛው መዋቅር እንዲወርድ በማሰብ በ14ቱም ወረዳዎች ለሚገኙ የ270 አብያተክርስቲያናት የደብር አስተዳዳሪዎች ፣የሰበካ ጉባኤ አባላት ፣የሰንበት ትምህርት ቤት እና የማኅበራት ተወካዮች የሚገኙበት ስልጠና የፊታችን መስከረም 18 እና 19 ለመስጠት ዝግጅት ላይ ይገኛል።

ታዲያ ይህንን ስልጠና ለሚሰጡ ምሁራንና የሀገረ ስብከቱ የየክፍል ኃላፊዎች ላለፉት ሁለት ቀናት ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል። በዚህ ስልጠና ቤተክርስቲያን ያለችበትን ደረጃ ለማወቅ የተጠናው ጥልቅ ጥናት ውጤት ተደራጅቶ ለውይይት የቀረበ ሲሆን ችግሮቻችን ሊፈቱ በሚያስችል ቁመና የ10 ዓመቱ መሪ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ለሰልጣኞች ተሰጥቷል።

ስልጠናውን የአሰልጣኞች ስልጠና ሲሆን የፊታችን መስከረም 18-19/2016 ዓ. ም በሁሉም ወረዳ የሚሰጠውን የአድባራት አመራር ስልጠና ለሚሰጡ ባለሙያዎችና የሀገረ ስብከቱ አመራር የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።

በዚህ ስልጠና 270 የድባራት አስተዳዳሪዎች 1,890 የሰበካ ጉባኤ አባላት፣540 የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች 724 ካህናትና ከ200 በላይ የማኅበራት ተወካዮች የሚገኙበት ሲሆን በድምሩ ከ3,624 ሰዎች የሚሳተፉበት ይሆናል።

በመርሐ ግብሩ ማጠቃላያ ላይ ንግግር ያደረጉና ስልጠናውን ላለፉት ሁለት ቀናት ሲመሩ የነበሩ የኢሉ አባ ቦር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ አባልና የመቱ ፈለገ ሕይወት መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ጠባቂ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ዶ/ር እንደተናገሩ ቤተክርስቲያናችን ከገባችበት ፈተና እንድትወጣ ከተፈለገ በዕቅድ መመራት ዋና መፍትሄ ሲሆን የታቀደው ዕቅድ በታቀደበት መንገድ እንዲፈጸም ከተፈለገደግሞ በሁሉም የቤተክርስቲያን መዋቅር ደረጃ የአፈጻጸም ሂደቱን መገምገምና መከታተል ቁልፍ ተግባር ሆኖ መቀጠል አለበት ብለዋል።

ብፁዕነታቸው አያይዘው እንደገለጹት ባለፉት ሁለት ቀናት ሀገረ ስብከቱ ያዘጋጀውን ስልጠና የወሰዳችሁ የቤተክርስቲያን ልጆች ተቋሙ ያወጣውን የ10 ዓመት መርህ ዕቅድ ለቤተክርስቲያን ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ተረድታችሁ ሕዝባችንን እንድታስገነዝቡልን አደራችን ጥልቅ ነው ብለዋል።

በስልጠናው ላይ የተገኙት ሰለሰጣኞች እንደተናገሩት ሀገረ ስብከቱ በዚህ መልክ የ10 ዓመት ስልታዊ ዕቅድ አውጥቶ በዚያ ለመመራት መወሰኑ ተስፋ ሰጭ ነው ብለው የሚመለከተው የቤተክርስቲያን አመራርና መላው በሀገረ ስብከቱ ውስጥ የሚገኙ ማኅበረ ካህናትና ማኅበረ ምዕመናን ለእቅዱ ተፈጻሚነት ሊሰለፉ ይገባል ብለዋል።

የዜናው ምንጭ የኢሉ አባ ቦር ሀገረ ስብከት ሕዝብ ግንኙነት ነው።