“የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከጠፋንበት አገኘችን” ትውልደ አሜሪካዊው ካህን
የ፵፪ ኛው አጠቃላይ ዓለም አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የሦስተኛ ቀን ውሎ የአኅጉረ ስብከቶችን ሪፖርት በማዳመጥ ላይ ይገኛል።
በዛሬው የሪፖርት ቀን ከሀገር ውስጥ አኅጉረ ስብከቶች በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ አኅጉረ ስብከቶች ሪፖርታቸውን ማቅረብ ጀምረዋል። በጉባኤው ላይ ከቀረቡት ሪፖርቶች መካከል አንዱ የሆነው የኒዮርክ እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሪፖርት ሲሆን ያቀረቡት ትውልደ አሜሪካዊው መልአከ ገነት ተስፋ ኢየሱስ ናቸው።
መልአከ ገነት ተስፋ ኢየሱስ በ1975 ዓ.ም በብፁዕ አቡነ ይስሐቅ አማካኝነት በሀገረ አሜሪካ ተጠምቀው የቤተ ክርስቲያን ልጅነትን ያገኙ ሲሆን በ1988 ዓ.ም ደግሞ ቅስናን ተቀብለዋል።
ባላቸው የአገልግሎት ትጋት እና የቤተ ክርስቲያን ፍቅር አማካኝነት በብፁዕ አቡነ ዘካርያስ መልአከ ገነት ተብለው በሀገረ አሜሪካ የደብረ ገነት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ተደርገው ተሹመዋል።
በአሁኑ ወቅት በደብሩ ውስጥ በቅስና የሚያገለግሉት እርሳቸው ብቻ ሲሆኑ ሁለት ዲያቆናት አብረዋቸው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
በዛሬው የአጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ በመገኘት የሀገረ ስብከቱን ሪፖርት በእንግሊዘኛ ቋንቋ ያቀረቡ ሲሆን በጉባኤው ላይ በመገኘታቸው ትልቅ ደስታን እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።
“እኛ ምዕራባውያን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፈልጋ እስክታገኘን ድረስ ጠፍተን ነበር አሁን ግን ከጠፋንበት አግኝታናለች” በማለት ለቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ፍቅር እና አክብሮት ገልጸዋል።
ጉባኤውም ትልቅ አድናቆት እና ክብር ሰጥቷቸዋል።