ጷጉሜ ፭ ቀን ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም
“”””””””””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
+++++++++++++
የጠቅላይ ቤተክህነቱ አስተዳደር ጉባኤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በቅርቡ የሰጠውን መግለጫ በተመለከተ በሰፊው ተወያይቶ ልዩልዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
አስተዳደር ጉባኤው ሀገረ ስብከቱ በሰጠው መግላጫ ላይ ሕግና ሥርዓትን አክብሮ እንዲሁም ከጠቅላይ ቤተክህነት ጋር በመመካከር የሚሰራ መሆኑን የገለጸበት ሁኔታ አግብነት የሌለውና ከግብረ ሙስና ጋር በተያያዘ በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ለተነሳበት ወቀሳ ከለላ ለመፈለግ የተሰጠ የሽፋን መግለጫ መሆኑን በማውሳት መግለጫውን በአጽንኦት ተችቶቷል።
ጠቅላይ ጽሕፈት ቤቱ በተለያዩ ጊዜያት ሀገረ ስብከቱ ሕግና መመሪያን አክብሮ ብቻ እንዲሰራ በተለያዩ ጊዜያት ልዩሎዩ መመሪያዎችን በተደጋጋሚ ሲያስተላልፍ መቆየቱን ያስታወሰው ጉባኤው ሀገረ ስብከቱ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሚተላለፍለትን የሥራ መመሪያ ወደ ጎን በመተውና በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ ሥራ ላይ የዋለውን የሀገረ ስብከቱን መተዳደሪያ ደንብ በመጣስ ልዩልዩ የሥራ ግድፈቶችን ሲፈጽም ከቆየ በኋላ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካላት በተደራጀ ሁኔታ እየተነሱበት ያሉትን ጥያቄዎች ለመሸሽ ሲል አላሰራ ብሎኛል በማለት ሲተቸው የከረመውን የሀገረ ስብከቱን መተዳደሪያ ደንብ እንደ መሸሸጊያ ለመጠቀም መሞከሩ እጅጉን አሳፋሪና እርባና ቢስ መሆኑን ጉባኤው ገልጿል።
ከሁሉ በላይ ጠቃሚ የሚሆነው ሕግና ሥርዓትን አክብሮ መስራት እንደሆነ የገለጸው ጉባኤው ሀገረ ስብከቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ ሥራ ላይ እንዲያውለው የተሰጠውን መተዳደሪያ ደንብ ወደ ጎን በማለት ያከናወናቸው ሕገ ወጥ ተግባራት በጊዜ እንዲታረሙ አለመደረጋቸው ቤተክርስቲያናችንን ለተጨማሪ ኪሳራና ለመልካም ስሟ መጉደፍ ምክንያት ሆኗል ብሏል።
በአሁኑ ጊዜ የሚታየውን የሙስና መስፋፋትና የመልካም አስተዳደር እጦት ያስከተለውን ብልሹ አሰራር አምረን ካልተቃወምንና የተሻለ ተቋማዊ የአሰራር ስርዓትን በመዘርጋት በሕግ፣በመመሪያና በደንብ የሚመራ ተቋም በመፍጠር
ቤተክርስቲያንን መታደግ ካልቻልን በእግዚአብሔርም በታሪክም በሕግም በሞራልም ከተጠያቂነት ስለማንድን ችግሩን በይፋ አውጥተን ዳግመኛ በማይደገምበት ሁኔታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍታት ይጠበቅብናል ያለው ጉባኤው የቤተክርስቲያንን መልካም ስም ወደ ቀደመ ክብሯ ለመመለስ ይቻል ዘንድ እስከ መጨረሻው በጽናት የሚጠበቅብንን ሁሉ እንሰራለን ብሏል።
በመሆኑም በሀገረ ስብከቱ የሚስተዋለውን የሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመሰረቱ መፍታት ይቻል ዘንድ በአጭር ቀናት ውስጥ ዝርዝር ጉዳዩን ከመፍትሔ ሀሳብ ጋር በማጥናት የሚያቀርብ ከጠቅላይ ቤተክህነት፣ከምሁራን፣ከወጣቶችና ከማኅበራት የተውጣጣ ጠንካራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ እንዲገባና በአስራ አምስት ቀናት ውስጥ አጥንቶ በሚያቀርበው ሰነድ መነሻነት ተቋማዊ ለውጥ ሊያስመዘግብ የሚያስችል ሥራ እንዲሰራ ወስኗል።
ይህንን ሥር ነቀል የአሰራርና አደረጃጀት ለውጥን ለማምጣት የሚደረገው ተጋድሎ ሀገረ ስብከቱንም ሆነ ቤተክርስቲያናችንን የሚጠቅም፣መልካም ስምና ልዕልናዋን የሚመልስ እንዲሆን በማድረግ የምዕመናንን እምነት በድጋሜ ማግኘት በሚያስችል ስልት በመምራት ለአፈጻጸሙም አስፈላጊውን መስዋዕትነትን ለመክፈል ቁርጠኛ መሆኑን የገለጸው አስተዳደር ጉባኤው ይህ ጉዳይ ግቡን እስከሚመታ ድረስ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪና እንደ አንድ ልብ መካሪ በጋራ የምንሰራ መሆኑን በአክብሮት እንገልጻለን በማለት ያለ ምንም ልዩነት በአንድ ድምጽ ወስኗል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም ያልተጠናና እውነትን መሰረት ያላደረገ መግለጫ በመስጠት ሕዝበ ክርስቲያኑን ያሳዘኑ የሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎችም ለፈጸሙት ተቋማዊ መናጋትና ላስተላለፉት በሐሰት ላይ ለተመሰረተ መረጃ በአስቸኳይ ተገቢውን ተመጣጣኝ የሆነ አስተዳደራዊ የእርምት ውሳኔ ሀገረ ስብከቱ በመስጠት ለጠቅላይ ቤተክህነት በሪፖርት እንዲገለጽ ጉባኤው ወስኗል።
በሌላ በኩል ከደመወዝ ጭማሪ ጋር ተያይዞ አስተዳደር ጉባኤው የሚከተለውን ውሳኔ አስተላልፏል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ሠራተኞችን ከአጥቢያ ወደ ሀገረ ስብከት አዛውሮ በሚመድብበት ወቅት በሠራተኛ መተዳደሪ ደንቡን አንቀጽ 8 ንዑስ ቁጥር 6 የሕግ ድንጋጌ መሠረት የቦታውን መነሻ በጀት እንዲያገኙ ማድረግ ሲገባው ሕጉ ተጥሶ አስቀድሞ በቦታው ላይ ይሠራ የነበረው ሠራተኛ በአገልግሎት ብዛት የሚያገኘውን ደመወዝ እንዲያገኝ መደረጉ አግባብነት የሌለውና የዋናው መ/ቤትም እንዲህ አይነቱን
ጥያቄ እየተቀበለ ሲያጸድቅ መቆየቱ የሠራተኛ መተዳደሪያ ደንቡን የጣሰ አድራጎት በመሆኑ ከዛሬ ነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እንዲህ አይነቱ ተግባር እንዳይፈጸም አስተዳደር ጉባኤ ወስኗል፡፡
ሀገረ ስብከቱ ከአጥቢያ በዝውውር ወደ ሀገረ ስብከቱ የሚዛወሩ ሠራተኞች በጀት በተመለከተ ከመደበኛ የደመወዝ በጀት ውጭ የፋይናንስ እና የሠራተኛ መተዳደሪያ ደንቡ ተጥሶ የነዳጅና የልማት ገቢ አበል በማለት የሚተከለው በጀት እንዲቆም፣ሀገረ ስብከቱ ያለምንም ሥራና በቂ ምክንያት በዝውውር በሀገረ ስብከቱ ውስጥ እየተገበረው ያለውን የሠራተኛ ክምችት እንዲያቆም፤ከክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት እስክ ሀገረ ስብክት ባሉት የሥራ መደቦች የሚፈጸም የሠራተኛ ቅጥር ዝውውር እና እድገት በሀገረ ስብከቱ መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 10 ንዑስ ቁጥር 4 እና በአንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ 1 ተራ ቁጥር 3 የሕግ ድንጋጌ መሠረት በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሲጸድቅ እና ሲፈቀድ ብቻ ይፈጸም በማለት ወስኗል።