መስከረም 27 ቀን 2017ዓ.ም.
+ + +
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የማኅበራት ምዝገባ፣ ክትትልና ቁጥጥር መምሪያ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በቤተክርስቲያናችን ሥር የተቋቋሙ መንፈሳዊያን ማኅበራትን በመመዝገብ፣በመከታተልና በመቆጣጠር የቤተክርስቲያናችንን ሕግጋት፣ መመሪያዎችና ሥርዓቶችን አክብረው እንዲሠሩ የማድርግ ኃላፊነትን ከተቀበለበት ጊዜ ጀምሮ ማኅበራትን በመመዝገብና በማደረጃት ሰፊ ሥራዎችን እየሠራ ቆይቷል።
በዚሁም መሠረት መምሪያው በይፋ ከተቋቋመና ወደ ሥራ ከገባ ወዲህ ለአሥራ ሰባት መነፈሳዊያን ማኅበራት ምዝገባ በማካሔድ ሕጋዊ እውቅናን በመስጠት ወደ ሥራ እንዲገቡ አድርጎል።
እነዚሁ ማኅበራትም ሕግና መመሪያን አክብረው እንዲሰሩ ማድረግ የሚቻልበትን የመመስረቻ ደንብና የምስክር ወረቀት የተሰጣቸው ሲሆን በቀጣይ በሚያስማማቸው፣በሚያግባባቸውና በጋራ ለአንዲት ቤተክርስቲያን ጥቅም በሚያሰሯቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተባብረው መስራት ይችሉ ዘንድ የውይይትና የምክክር መድረክ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ይህ የውይይትና የምክክር መድረክ በመምሪያው በኩል እንዲዘጋጅ አደርጓል።
በውይይትና በምክክር መድረኩም በማኅበራቱ መካከል መግባባት፣መናበብና በጋራ መስራትን በመፍጠር ረገድ ጉልህ ድርሻ ያለው እንዲሆን ሰፊ ምክረ ሐሳብ ቀርቧል። ውይይቱን በበላይነት የሚመሩት የመምሪያው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ይህ የውይይት መድረክ የተዘጋጀው ማኅበራቱ የጋራ እሴት ኖሯቸው እንዲሠሩ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል። በውይይቱ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ የባሕርዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ አብርሃምን ጨምሮ በርካታ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፣ የመንበረ ፓትርያርክ የየመምሪያው ኀላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው ፈቃድ የወሰዱ ማኅበራት ተገኝተዋል።
ውይይቱ ከሰዓች በኋላም የሚቀጥል ሲሆን ማኀበራት በብዙ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ እውቀት እንደሚቀስሙ ይጠበቃል።