ሐምሌ ፲፮ ቀን፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም
“”””””””””””””””””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
*****

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአራት ኪሎ እና ፒያሳ የምታስገነባቸው አዳዲስ ሁለገብ ሕንጻዎች የንድፍ ሥራቸው ተጠናቅቆ ርክክብ ተካሄደ፡፡

አራት ኪሎ ላይ የሚገነባው በ6,000 ካሬ ላይ የሚያርፍ ባለ 12 ወለል ሕንጻ ሲሆን፤ እስከ 4ኛው ወለል ለንግድ አገልግሎት፣ ቀሪው ደግሞ ለመኖሪያነት ያገለግላል፡፡ በተመሳሳይ በፒያሳ የሚገነባው በ1,686 ካሬ ላይ የሚያርፍ ባለ 7 ወለል ሕንጻ እስከ 3ኛው ወለል ለንግድ አገልግሎት፣ ቀሪው ደግሞ ለመኖሪያነት እንዲያገለግል ታስቧል፡፡

የሕንጻዎቹን ንድፍ ኢ ኢ ኤስ ኮንሰልቲንግ አርክቴክት እና ኢንጂነሪንግ ፒ ኤል ሲ በተባለ ድርጅት ተካሂዶ፤ ብፁዕ አቡነ ሣዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተረክበዋል፡፡

በርክክብ መርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ የሕንጻዎቹ የንድፍ ሥራ በመጠናቀቁ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ለሥራው የደከሙትን ሁሉ አመስግነዋል፡፡ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ‹‹ከዚህ በኋላ ወደ ሥራ ለመግባት ምንም የቀረ ነገር የለም ፤ ወደፊት ነው እንጂ ወደ ኃላ የለም” ሲሉ የሕንጻ ግንባታውን ለመጀመር በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በኩል ያለውን ቁርጠኝነትና ዝግጁነት አስታውቀዋል፡፡

በርክክብ ሥነ ስርዓቱ ላይ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ፣ የማይጨው አላማጣና ራያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም የጠቅላይ ቤተክህነት ልዩ ልዩ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልዕክት የንድፍ ሥራው ለግንባታው ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ጠቅሰው፡- ‹‹ሥራው በመጠናቀቁ እድለኞች ነን፡፡ አባቶቻችን በሥጋ ሳይሆን በነፍስ ተጠቃሚ ሁነው፤ ያቆዩልንን ሐብት፤ ቤቶች፤ መሬት፤ እኛም ቤተክርስቲያኗን የተረከብን የዚህ ዘመን ትወልድ አልምተን ለቀጣዩ ትውልድ ለማሸጋገር እንሠራለን›› ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡

የሕንጻዎቹ ዲዛይን ከዘመናዊነት ባለፈ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ትውፊት የተላበሱ እንዲሆኑ ተደርጎ መዘጋጀቱ በመርሐ ግብሩ ላይ ተገልጿል፡፡ በአራት ኪሎ እና ፒያሳ የሚገነቡት ሁለቱ ሁለገብ ሕንጻዎች “ሕንጻ አበው” እና “ዝክረ ቅዱሳን” ተብለው የተሰየሙ ሲሆን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡