ነሐሴ ፳፬ ቀን ፳፻ ፲፭ ዓ.ም
******
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰሜን አሜሪካን በሲራኪዮስ ከተማ በምትገኘው የገነተ ደናግል ቅድስት አርሴማ ወክርስቶስ ሰምራ ገዳም ተገኝተው በገዳሙ የአብነት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ለቆዩ አራት ተማሪዎች የዲቁና ማእረግ በመስጠት አባታዊ መመሪያን አስተላልፈዋል።
ገዳሙ በ፳፻፬ ዓ/ም በሥርዓተ ቤተክርስቲያን የተገደመና በሰሜን አሜሪካን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እየሰጠ ያለ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመጀመሪያው ገዳም ነው።
ገዳሙ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ምዕመናን፣ ካህናትና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ሠፊ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚያገኙበትና በታመሙና በተጨነቁ ጊዜ ሁሉ ወደ ገዳሙ በመጓዝና ሱባኤን በመያዝ እግዚአብሔርን በመማጸን መንፈሳዊ ፈውስን ከእግዚአብሔር የሚቀበሉት ቅዱስ ስፍራ ነው። ሕጻናትና ወጣቶችም በገዳሙ አድገውና የቤተክርስቲያንን የአብነት ትምህርትቶች ተምረው ለነገዋ ቤተክርስቲያን ተተኪ አገልጋዮች የሚሆኑበት እድልም ተፈጥሯል። በማኅበራዊ ዘርፍም በልዩልዩ ምክንያቶች መግባባት የተሳናቸውና የተጋጩ ምዕመናን በሽምግልና ችግሮቻቸውን የሚፈቱበት ሁኔታም በገዳሙ ተመቻችቶ ውጤታማ ሥራ እየተሠራ ይገኛል።
ገዳሙ የሰሜን አሜሪካ ሥልጣኔ የሚፈጥራቸውን በጎ ያልሆኑ ተጽዕኖዎች ተቋቁሞ ከፓለቲካዊና ዘረኝነት አስተሳሰብ በጸዳ መልኩ አገልግሎቱን በመፈጸም ረገድ የሚያደርገው እንቅስቃሴም የሚመሰገንና በሌሎች የአገሪቱ ግዛቶችም ሊለመድ የሚገባው በጎ ተግባር ነው እያሉ በገዳሙ መንፈሳዊ አገልግሎት ያገኙ በርካታ ምእመናንን ሀሳባቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።
በዚሁ ገዳም አስተባባሪነት የአብነት ትምህርታቸውን ተከታትለው ለአገልግሎት ለተዘጋጁ ተማሪዎች ለሢመተ ዲቁና ከተመረጡበት ቀን ጀምሮ እስከሚሾሙበት ጊዜ ድረስም በኪዳንና በቅዳሴ ጸሎት ላይ ስማቸው እየተጠራ ይጸለይላቸዋል።
ከመሾማቸው አስቀድሞ ለዲያቆናቱ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ሥልጠና ይሰጣቸዋል። ሹመቱ ከተፈጸመላቸው በኋላም በምዕመናን ፊት ቃል ይገባሉ።
በ፳፻፲፭ ዓ/ም የደብረ ታቦር በዓል ላይ የተገኙት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከፍ ሲል በተገለጸው መልኩ ሥርዓተ ዲቁና ለመቀበል ለተዘጋጁ አራት ተማሪዎች የዲቁና ማዕረግ ሰጥተዋል። ከዲያቆናቱ መካከልም የቤተክርስቲያንን የአብነት ትምህርት በሚገባ የተማሩና ወደ መዘምርነት የተቃረቡ፣ ቅዳሴ፣ ሰዓታት፣ በሥርዓተ ማኅሌት መሳተፍ እንዲሁም ቅኔ መመራትን የቻሉ ተማሪዎች ይገኙበታል።
ከዚህም በተጨማሪ ሁሉም ዲያቆናት በወጣላቸው መርሐ ግብር መሠረት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ይሰብካሉ።
ይህን አገልግሎት የተመለከቱት ብፁዕ (ዶ/ር) አቡነ ጴጥሮስም ገዳሙ ሊጠናከር፣ ሊስፋፋና ተገቢው ድጋፍ ሁሉ ሊደረግለት እንደሚገባ የገለጹ ሲሆን በሰሜን አሜሪካን ተተኪ አገልጋይ መሆን የሚችሉ ዘመኑን የዋጁና ሰይፍ በክልኤ የሆኑ አገልጋዮችን የማፍራቱን
ሂደትም አጠናክሮ እንዲቀጥል አደራ በማለት አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።