ጥቅምት ፲ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
****
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
“””””””””””””””””””””

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመገናኛ ብዙሃን ሥርጭት ድርጅት EOTC TV ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ በሚዲያው ዘርፍ ብቁና ተመራጭ የሚያደረጉትን ተግባራት በማከናወን ላይ ይገኛል። ለዚህም ራሱን በሰለጠነ የሰው ኃይልና ቁሳቁስ በማደራጀት የተጣለበትን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት የሚያስችሉትን ተግባራት በትጋት በማከናወን አሁን የሚገኝበት ቁመና ላይ ደርሷል።

በተለይም ሊቀ ማዕምራን ፈንታሁን ሙጨ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ሆነው ከተመደቡ ወዲህ ከድርጅቱ ሊቀ ጳጳስ ከብፁዕ አቡነ ማቴዎስ መመሪያን በመቀበልና በመመካከር ድርጅቱ በብቃትና በጥራት ቤተክርስቲያንን ማገልገል የሚያስችለው አቋም ላይ እንዲገኝ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ የሚታዩና የሚዳሰሱ ውጤቶችን አስመዝግበዋል።

ከእነዚህ ውጤታማ ሥራዎች መካከልም ድርጅቱ የሚገለገልባቸው ቢሮዎችና ቅጽረ ጊቢው ለቀረጻና ለሚዲያ ሥራ ምቹ እንዲሆን የማድረግ ሥራ በሚገባ በማከናወን ድርጅቱን ውብ፣ማራኪ፣ለሚዲያ ሥራ ምቹና ተመራጭ የማድረግ ሥራን አከናውነዋል።

በዚህም የድርጅቱ ቢሮዎችና ቅጽረ ጊቢው የቤተክርስቲያንን ከብር በሚመጥን መልኩ እንዲደራጅና እንዲዋብ ከማድረጋቸውም በላይ የተደራጁና ለሥራ ምቹ የሆኑ ስቱዲዮዎች፣ካሜራዎች፣የድምጽ ግበዓቶችና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች እንዲሟሉለት አድርገዋል።

የሰራተኛውን የማስፈጸም ብቃትና የሥራ ተነሳሽነትን ለመጨመርም ልዩልዩ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን በዘርፉ በሰለጠኑ ባለሙያዎች ለሰራተኞቹ እንዲሰጥ በማድረግ የድርጅቱ ሥራ ውጤታማ የሚሆንበትን ተግባር አከናውነዋል።

አሁን ደግሞ ለድርጅቱ ሥራ መቀላጠፍ ሲባል የሁለት ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን ግዥ በመፈጸም በትራንስፖርቱ ዘርፍ የሚታየውን ክፍተት በመሙላት የድርጅቱ ሥራ የበለጠ የሚጠናከርሰበትን ሁኔታ ፈጥረዋል።ከዚህ ጎን ለጎንም የድርጅቱ ሥራዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የታገዙ እንዲሆን ለማድረግ ዘመናዊ ካሜራዎችን ፣ዘመናዊ የሰዓት መቆጣጣሪያ ማሽንና ኮምፒዩተሮችን በማሟላት በሥራውና በሰራተኛው መካከል ከፍተኛ መነቃቃት እንዲፈጠር አድርገዋል።

ሊቀ ማዕምራን ፈንታሁን ከዚህ ቀደም በመሯቸው ተቋማት ሁሉ ተመሳሳይ ተግባራትን በመከወን ሥኬታማ ሥራን ያከናወኑ የሥራ መሪ መሆናቸው ይታወቃል።