ጥር ፴ ቀን ፳፻፲ወ፮ ዓ/ም አዲስ አበባ።
+ + +
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በየዓመቱ የሚያካሂደውንና ወዘቅታዊና ዘላቂ የቤተክርስቲያናችን ጉዳይ ላይ በየዓመቱ የሚያደርገውን የሁለት ቀናት የሥልጠናና የውይይት መርሐ ግብር ዛሬ ጥር ፴ ቀን ፳፻፲ወ፮ ዓ/ም ጀመረ።
“ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ” (ፊል.፩፥፳፯) የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት የጉባኤው መሪ ቃል ያደረገው መምሪያው ስብከተ ወንጌል የቤተክርስቲያናችን ዋና ተልእኮ ከመሆኑ አንጻር ከፍተኛ ትኵረት ተሰጥቶት ዘመኑን የዋጀ የስብከተ ወንጌል ተደራሽነትን ማረጋገጥ፣ የቅድስት ቤተክርስቲያንን መዋቅራዊ ትሥሥር ማጠናከርና የአገልጋዮችን አእምሮአዊና መንፈሳዊ ክሂሎት ላይ አበክሮ ለመሥራት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የመምሪያው ኃላፊ መ/ሰ. ቆሞስ አባ ቃለጽድቅ ሙሉጌታ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
መርሐ ግብሩን በጸሎት የከፈቱትና አባታዊ መልእክታቸውን ያስተላለፉት የመምሪያው የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ “ከሁሉ በፊት የምንሰብከውን የወንጌል እውነት እንኑረው፤ ከዚያ በኋላ ሁሉም ይከናወንልናል፤ ችግር እየገጠመን ያለው የምንሰብከውን ባለመኖራችን ነው፤” ሲሉ መልእክታቸውን በማስተላለፍ ውይይቱ ተግባር ተኮር እንዲሆን አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል።
በዛሬው መርሐ-ግብር ላይ ዕቅበተ እምነትንና በአገልግሎት ላይ የሚፈጠሩ ተግዳሮቶችን እንዴት ማለፍ ይገባል በሚል ርእሰ ጉዳይ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የዕለቱን መርሐ-ግብር በጸሎት እንዲከፍቱና አባታዊ መልእክት እንዲያስተላልፉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት እቅድ ይዘው የነበረ ቢሆንም በወቅታዊ ጉዳይ የመርሐ-ግብር መደራረብ ምክንያት ሳይገኙ ቢቀሩም አባታዊ መልእክታቸውን በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በኩል አስተላልፈዋል። የብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አባታዊ መልእክትም በክቡር ምክትል ሥራ አስኪያጅ በኩል ተላልፏል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ የኢትዮ ሱማሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ቶማስ የአዊና መተከል አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ሊቀ አእላፍ በላይ መኮንን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የመምሪያና የድርጅት ኃላፊዎች፣ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ የክፍለ ከተማ አብያተ ክህነት የስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊዎችና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራትና የገዳማት የስብከተ ወንጌል ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የመርሐ-ግብሩ አስፈላጊ ወጪዎች በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበርና በአሐዱ ባንክ አ.ማ. መሸፈኑ በመምሪያው ተገልጿል።