ጥር ፭ ቀን ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም
++++++++++++++++++
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
“”””””””””””””””””””””
ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ከሦስት ዓመት በፊት ወደ ሰሜን አሜሪካ ለሥራ ባመሩበት ወቅት በአካባው ለሚገኘው የኋለኛው ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት፤ የተጠቀሰው ቤተ ዕምነት መሪዎች ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ምእመናን መገልገያ የሚሆን ከ6 ሺ ካሬ ሜትር በላይ የሆነ መሬት ሊያበረክቱ ችለዋል፡፡

የዚህም ማምለኪያ ሥፍራ ካርታና ፕላን ጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳርና ሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት፤ የሰላም ምንስቴር ሚንስትር ዲኤታ ክቡር ከይረዲን ተዘራ ዶ/ር፣   የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንዲሁም የኋለኛው ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ተወካዮች፣ በመንበረ ፓትርያክ በመገኘት ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አስርክበዋል፡፡

የመንግሥት አካላት በተለይም የሰላም ሚንስትር የነበሩት አቶ ብናልፍ አንዱዓለም በቦታው ርክክብ ሂደት ከፍተኛ እገዛ ማድረጋቸውን በዕለቱ የተገለጸ ሲሆን በዩነታሃ ግዛት ሰፊውን አማኝ ያላት የኋለኛው ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አመራሮች ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባበረከቱት የማምለኪያ ሥፍራ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ለቅዱስነታቸው በሰጡት ማብራያ አስታውቀዋል፡፡

በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ በተደረገው ነገር መደሰታቸውን ገልጸው ይህንን ላደረጉ አካላት ምስጋና ይገባቸዋል በማለት አባታዊ ቡራኬያቸውን አስተላልፈዋል፡፡