የከተራ በዓል ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በተገኙበት በጃን ሜዳ በታላቅ ድምቀት ተከበረ

ጥር ፲ቀን ፳፻ ፲ወ፭ዓ.ም
“”””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
“””””””””””””””””””””

የ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም የከተራ በዓል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በተገኙበት በጃንሜዳ ባህረ ጥምቀት በታላቅ ሥነሥርዓት ተከብሮ ውሏል።በበዓሉ ላይ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒዩወርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ፣ክቡር ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን፣የጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች፣በተገኙበት ነው የተከበረው።

በጃን ሜዳ ባህረ ጥምቀት የባለተራው የደብር ደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስና ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ሊቃውንት መሪነት”ወረደ ወልድ እምሰማያት”በቁም ዜማ በዝማሜና በጸናጽል ከዘመሩ በኋላበፍስሐ ወበሰላም የሚለውን አመላለስ ለ፴ ደቂቃ ያህል አሸብሽበዋል።

በመቀጠልም የደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስና ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ፍቁረ እግዚእ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች “ወነዋ ተወልደ ወነዋ ተጠምቀ መድሃኔ ዓለም። ፍሥሐ ለከኲሉ ኲሉ ዘየአምን”የሚለውን ለ፲፭ ደቂቃ ወረብ አቅርበዋል ።

በመጨረሻም ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቃለ ምዕዳንና ጸሎተ ቡራኬ ከሰጡ በኋላ ታቦታቱ ወደ ተዘጋጀላቸው ድንኳን ገብተው የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።