በሰሜን አሜሪካ በዴንቨር ከተማ በዛሬው ዕለት የሀገረ ስብከቱ ፮ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መካሔድ ጀመረ። በ፮ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ የተገኙት የዴንቨር ኮሎራዶና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ጉባኤውን በፀሎት የከፈቱት ሲሆን ጉባኤውንም በርዕሰ መንበርነት እየመሩት ይገኛሉ።
የጉባኤው ርዕሰ መንበር ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የ፮ኛውን አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤውን ዓላማ በማስመልከት አባታዊ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት ሀገረ ስብከቱ በየዓመቱ በመንፈሳዊ አገልግሎት ዘርፍ የሚያስመዘግባቸውን ተግባራት የበለጠ በማጠናከር ተጨማሪ ውጤቶችን ማስመዝገቡን እንዲቀጥል አደራ በማለት አባታዊ መመሪያ በመስጠት ጉባኤውን በይፋ ከፍተዋል።
ጉባኤውም በዛሬው እለት ውሎው በሀገረ ስብከቱ ስር የሚገኙ አድባራትና ገዳማትን ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ሲያዳምጥ የዋለ ሲሆን በነገው እለት የጉባኤው ውሎም የሀገረ ስብከቱንና የቀሩ አብያተ ክርስቲያናትን ሪፖርት እንደሚያዳምጥ፤ በተሰሙት ሪፖርቶች ዙሪያ ውይይት ካደረገ በኋላ ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥና የአቋም መግለጫ በማውጣት ጉባኤውን እንደሚያጠናቅቅ ከሀገረ ስብከቱ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።