የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባኤ ሃይማኖታዊ ክህደት ፣ ቀኖናዊ ጥሰት እናአስተዳደራዊ ግድፈት የታየበትን የወሊሶውን ሹመት አወገዘ ቅዱስ ሲኖዶስ ተገቢውን ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ምዕመናን በጸሎት እንዲቆዩ አሳሰበ

********
ጥር ፲፭ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም
******
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
“”””””””””””””””””””

የጠቅላይ ቤተክህነት አስተዳደር ጉባኤ ዛሬ ጥር ፲፭ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም በሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን የጠቅላይ ቤተክህነት ም/ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰብሳቢነት ባካሔደው አስቸኳይ ጉባኤ ሃይማኖታዊ ክህደት ፣ ቀኖናዊ ጥሰት እናአስተዳደራዊ ግድፈት የታየበትን የወሊሶውን “ሹመት” አወገዘ ቅዱስ ሲኖዶስ ተገቢውን ውሳኔ እስኪሰጥ ምዕመናን በጸሎት እንዲቆዩ አሳሰበ።

ጉባኤው በቤተክርስቲያን ላይ በተፈጸመው ሁሉን አቀፍ ክህደት ዙሪያ ሰፊ ውይይት ያደረገ ሲሆን ክህደቱን የፈጸሙት አካላት ሥልጣን የሰጣቸውን መዋቅር (ተቋም) በመካድ የፈጸሙት ድርጊት እጅጉን አሳዛኝ ነው ብሏል።
የተፈጸመው ጉዳይም ህገ ወጥና ቤተክርስቲያንን የማፍረስ ወንጀል ነው ያለው አስተዳደር ጉባኤው በምንም መመዘኛ ይህን ከፈጸሙ አካላት ጋር መደራደር በተዘዋዋሪ የቤተክርርቲያናችንን ሕግና ሥራዓትን ማፍረስ ነው ብሏል።

በማያያዝም ጎሰኝነት ኑፋቄ መሆኑን የገለጸው አስተዳደር ጉባኤው ይህን በመሰለ ተመሳሳይ ጉዳዮች ዙሪያ በተለያዩ ጊዜያት የተጸሙ ክህደቶች በዓለም አብያተ ክርስቲያናት ተነቅፏል ካለ በኃላ በቋንቋ መማና ማስተማር ችግር እንዳልሆነ በመረዳት ቤተክርስቲያን በተለያዩ ቋንቋዎች የሚያስተምሩ አባቶችን በመሾም አገልግሎት እንዲሰጡ ስታደርግ መቆየቷን ሕገ ወጥ ድርጊቱን ከፈጸሙ አካላት በላይ ማስረጃ አይኖርም ብሏል።

ጉባኤው ለቅዱስ ሲኖዶስ የውሳኔ አካል ሊሆኑ የሚችሉ የውሳኔ ሀሳቦችን ከቀኖና ቤተክርስቲያን እና ከሕግ አንጻር በመነሳት የጠቆመ ሲሆን የተፈጸመው ክህደት ከቀኖና ቤተክርስቲያንና ከሕግ አንጻር አንዴት እንደሚገለጽ የሚያመለክት ሰፊ የሚዲያ ሥራ እንዲሰራ በመወሰንና በቂ ማብራሪያ የሚሰጡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንን በመመደብ ከዛሬ ጀምሮ ሁሉም ቋንቋዎች ማብራሪያ እንዲሰጥ ወስኗል።

ሁሉም የቤተክርስቲያናችን መዋቅር ተቋማቱን በንቃት መጠበቅና ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚተላለፍ መመሪያን በትጋት መጠበቅ እንደሚገባና አስፈላጊው መመሪያ በአስቸኳይ እንዲተላለፍ የወሰነው አስተዳደር
ጉባኤው በቤተክርስቲያን ላይ ክህደት የፈጸሙ
አካላት ወይም የሿሚና ተሿሚ ነን ባዮች ደመወዝ እንደ አስፈላጊነቱ እንዲታገድ፣በተቋማችን ውስጥ የሚገለገሉባቸው ቢሮዎችና ማረፊያ ቤቶች በአገግባቡ እንዱቀበጠቁ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን መንግስትም እያደረገ ያለውን ቤተክርስቲያንን የመጠበቅ ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጉባኤው ጠይቋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ምዕመናንና ምዕመናት ከጸሎት በተጨማሪ መዋቅራዊ መመሪያዎችን በትዕግስት እንዲጠብቁ አደራ በማለት የእለቱን ስብሰባ በጸሎት አጠናቋል።