መጋቢት 23/2016 ዓ.ም
“””””””””””””””””””””””
አዲስ አበባ- ኢትዮጵያ
******

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የጽርሐጽዮን ዘተዋሕዶ የሐዋርያት አንድነት ኑሮ ማኅበር የሰባክያነ ወንጌልና የአብነት ትምህርት ማሠልጠኛ ማዕከል የ 32ኛ ዙር የበጋ ሠልጣኞች ምረቃና  እና ለቀጣይ ሥልጠና  የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐግብር ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የደቡባዊና ደቡባዊ ምሥራቅ ትግራይ አህጉረ ስብከት፣ በኢ/ኦ/ተ/ቤ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የቤተ መጻሕፍት ወመዘክር እና የማኅበራት ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ  ዩንቨርሲቲ አዳራሽ አከናውኗል

የጽርሐጽዮን ዘተዋሕዶ የሐዋርያት አንድነት ኑሮ ማኅበር የሰባክያነ ወንጌልና የአብነት ትምህርት ማሠልጠኛ  ለቤተክርስቲያን  ዘቢብ ጧፍ   ጥላ  ሻማ ብቻ ሳይሆን ሰውንም እንስጥ በሚል  መሪ ቃል የተቋቋመ ማሰልጠኛ ማዕከል  እንደመሆኑ መጠን ከልዩ ልዩ አህጉረ ስብከቶች የተወጣጡ ሰልጣኞችን  በየቋንቋቸው አሰልጥኖ አስመርቋል።

በዛሬው ዕለት 59 ተማሪዎች ከ 21 አህጉረ ስብከት የተወጣጡ ሲሆን 20 በሚደርሱ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች መሰልጠናቸው በመርሐ ግብሩ  ላይ ተገልጿልተገልጿል።

በምረቃው ላይም በማኅበረ ቅዱሳን አባላት የበገና ዝማሬን ፣ በመጋቤ ሐዲስ ወልደ ትንሣኤ ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቷል  እንዲሁም ማኅበሩ  አስተምሮ ለምረቃ ካበቃቸው ተመራቂ ተማሪዎች  መካከል በአማርኛ ፣ ኦሮምኛ ፣ሃድይኛ ፣ ማሊኛ ፣ዴምኛ ፣ ቤንችኛ ቋንቋዎች ጣዕመ ዝማሬ ቀርቧል።

ማኅበሩ ከሀገር ውስጥ ቋንቋዎች በተጨማሪ በውጭ ቋንቋዎች በእንግሊዝኛ ፣ ጀርመንኛና ሱዋህሊኛን ጨምሮ በ77 ቋንቋዎች 2,116 ደቀ መዛሙርትን በማስተማር  ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ነፍሳትን ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መልሷል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስን ጨምሮ በርካታ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ፣ ተመራቂ ተማሪዎች እና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።