ሰኔ፲፬ቀን ፳፻ ፲ወ፭ዓ.ም
“”””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
******

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፖትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያና የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ በጋራ የሚያስተባብሩት በስብከተ ወንጌል ማስፋፋትና በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አደረጃጀት ዙሪያ በ፵፰ አህጉረ ስብከት ሥልጠና ለመሥጠት ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ።

ዛሬ ሰኔ ፲፬ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ/ም በመንበረ ፖትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽርሐ ተዋሕዶ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በሥምሪቱ ተሳታፊ ለሆኑ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በሁለቱም መምሪያዎች ስለተዘጋጀው የሥልጠና ሠነድ እና ዕቅበተ እምነትን አስመልክቶ የተዘጋጀው መርሐ ግብር በብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒው ዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ እና በብፁዕ አቡነ ማርቆስ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ጸሎትና አባታዊ የመግቢያ መልእክት ተጀምሯል።

በየመምሪያዎቹ የተዘጋጁትን መርሐ ግብሮች አስመልክቶ ክቡር መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ቃለጽድቅ ሙሉጌታ (ዶ/ር) የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ዋና ኃላፊ እና በክቡር ሊቀ ኅሩያን መሐሪ አስረስ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ዋና ኃላፊ ገለጻ ተደርጓል።

ከዚህ ቀደም የሁለቱ መምሪያዎች የአገልግሎት ሥምሪቶቹን በተናጠል ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆንም በዚህ ዓመት የተሻለ ውጤት ለማምጣት ሲባል በጋራ ለመሥራት ባደረጉት ስምምነት መነሻነት የጋራ ስምሪቱ ዕቅድ ተዘጋጅቷል ።

ሥምሪቱ የሚደረገው ከሰኔ ፲፭ -፳፭ ቀን ፳፻ ፲ ወ፭ ዓ.ም ሲሆን በእቅድ በተያዙ ፴፰ አህጉረ ስብከት ትምህርትና ሥልጠናውን የሚሰጡ ፸፯ አገልጋዮች በሁለቱም መምሪያዎች በጋራ ተመድበዋል።