መስከረም ፲፭ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
“””””””””””””””””””””””””'”””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
***
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ከምታከብራቸው የአደባባይ በዓላት መካከል አንዱና በዓለም አቀፉ የትምህርት ሳይንስና ባህል ጅርጅት በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው የመስቀል ደመራ በዓል በነገው ዕለት በመስቀል አደባባይ በታላቅ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ይከበራል ።
ቅድስት ቤተክርስቲያናችን የ፳፻ ፲ወ፮ዓ.ም በዓልን በደመቀ መልኩ ለማክበር ይቻል ዘንድ ከአሥራ ሦስት በላይ ንዑሳን ኮሚቴዎችን በማደራጀት ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመተባበር ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን ስታደርግ ሰንብታ እነሆ ለዛሬው ዕለት ደርሳለች።የበዓል አከባበሩን የቅድመ ዝግጅት ሥራን በተመለከተም ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒዮወርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ዛሬ ከቀትር ቀኋላ በመስቀል አደባባይ በመገኘት የቅድመ ዝግጅት ሥራው የደረሰበትን ደረጃ ተዛውረው የጎበኙ ሲሆን አጠቃላይ የዝግጅት ሥራው በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተለይም የክብር እንግዶች የሚቀመጡበትን የመቀመጫ መድረክ ከነ ሙሉ የድምፅ ግብዓቱ በማቅረብ ለበዓላችን ድምቀት ትብብር ያደረገልንን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርንና ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤን አመስግነዋል።
የበዓሉን አከባበር ሥነ ሥርዓትን በተመለከተ በተዘጋጀው መርሐ ግብር መሠረትም በዓሉን ለማክበር ወደ መስቀል አደባባይ የሚመጡ ምዕመናንም ከጠዋቱ አምስት ሰዓት ጀምሮ ነጫጭ ልብስ በመልበስ ወደ በመስቀል አደባባይ መገኘት የሚኖርባቸው ሲሆን፣ የመንግሥት የጸጥታ አካላት በዓሉን ሰላማዊ በሆነ መልኩ ለማክበር ሲባል ለሚያደርጉት ፍተሻ ፍጹም ክርስቲያናዊ የሆነ ትብብር እንዲያደርጉ እናሳስባለን።
በአንዳንድ የመገናኛ አውታሮች የቤተክርስቲያን ንዋያተ ቅድሳት የሆኑ ከበሮ፣ጸናጽልና መቋሚያ እንዳይገባ ተከልክሏል በማለት የሚናፈሰው ወሬም ፍጹም ሐሰት መሆኑን እየገለጽን በዓሉን በትርኢት ለማክበር የተፈቀደላቸው ካህናትና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ኤነዚሁኑ ንዋያተ ቅድሳት ይዘው የሚገኙ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
በላላ በኩል ወደ በዓሉ ማክበሪያ በሚደረግ ጉዞ ላይ በአደባባዩ የሚገኙ የበዓሉ ታዳሚ ምዕመናን ያለምንም መግቢያ ባጅ ተፈትሸው ብቻ ወደ አደባባዩ መግባት የሚችሉ ሲሆን የመግቢያ ባጅ የሚጠየቁት የክብር እንግዶች፣ጋዜጠኞችና ልዩልዩ የሚዲያ ተቋማት ብቻ መሆኑን እንገልጻለን።
በመጨረሻም በዓላችን በአማረና ቀደመቀ መልኩ መከበር ይችል ዘንድ በማንኛውም መሌኩ ትብብር ላደረጉ አካላት በሙሉ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ምስጋናዋን ታቀርባለች።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
መሰከረም ፲፭ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ