የ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም የጌታችን፣ የአምላካችን፣ የመድኀኒታችን፣ የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል ሰላማዊ በሆነ መልኩ ተከብሮ እንዲውል ላደረጋችሁ ሁሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምስጋናዋን ታቀርባለች፤
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም የጌታችን፣ የአምላካችን፣ የመድኃኒታችን፣ የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም ተከብሮ እንዲውል ለማድረግ ልዩ ልዩ ኮሚቴዎችን በማቋቋም ስትሠራ የሰነበተች ሲሆን ከሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል መንግሥታትና የጸጥታ አካላት ጋርም በመነጋገር በዓሉ ያለ አንዳች የጸጥታ ችግር ተከብሮ እንዲውል ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ስታደርግ ሰንብታለች።
በዚህም መሰረት የከተራ፣ የጥምቀት፣ የቃና ዘገሊላ፣ የቅዱስ እግዚአብሔር አብ እና የቅዱስ ሩፋኤል በዓላት ፍጹም ሰላማዊና ሃይማኖታዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ በተረጋጋ፣ መንፈሳዊ በሆነና ፍጹም ክርስቲያናዊ ግብረ ገብነትን በጠበቀ ሁኔታ በመላ አገራችን ተከብሮ ውሏል። በተለይም በአዲስ አበባ በጃን ሜዳ በማዕከል ደረጃ የተከበሩት በዓላት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቀ አእላፍ በላይ መኮንን የጠቅላይ ቤተክህነት ምክትል ሥራአስኪያጅ፣ የፌደራልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣የጠቅላይ ቤተክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች፣ ሊቀ ማዕምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የዋና ክፍል ኃላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች፣ በሚሊየን የሚቆጠሩ ምእመናንና ምእመናት በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ውሏል።
የ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም የጥምቀት በዓል በዚህ መልኩ ባማረና በደመቀ ሁኔታ ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ ምዕመናንና ምዕመናት እንዲሁም ወጣት የቤተክርስቲያን ልጆቻችን የቤተክርስቲያንን ድምጽ በመስማትና በማክበር ላደረጋችሁት ከፍተኛ ጥረት ቅድስት ቤተክርስቲያን ምስጋናዋን ታቀርባለች። በዓሉ ያለምንም የጸጥታ ችግር ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ ቀን ከሌሊት የጸጥታውን ሥራ በማከናወንና አመራር በመስጠት፣ የትራፊክ ፍሰቱ በዓሉን በማያውክ መልኩ እንዲከናወን ያደረጋችሁ የከተማችን አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች፣ የጸጥታ አካላቱ አመራሮችና የጸጥታ መዋቅሩ አባላት እንዲሁም የትራፊክ ፓሊስ አመራሮችና አባላቱ ላበረከታችሁት አስተዋጽኦ ቅድስት ቤተክርስቲያን ልባዊ ምስጋናዋን ታቀርባለች።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት አዳነች አቤቤ በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲውል ለሰጡት አመራርና በዓሉ በተከበረበት በጃንሜዳ ደረጃውን የጠበቀ ስቴጅ፣ የድምጽ መሣሪያ፣ የክብር እንግዶች ወንበርና ለበዓሉ ድምቀት የሚያስፈልገውን ሁሉ በማሟላትና ወጪውን በመሸፈን በዓሉ አገራዊ መሆኑን በተግባር በማሳየት ላደረጉልን ድጋፍ በድጋሚ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ልባዊ ምስጋናዋን ታቀርባለች።
በአጠቃላይ የ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም የጥምቀት በዓላችን ፍጹም መንፈሳዊና ደማቅ በሆነ መልኩ ተከብሮ እንዲውል ልዩ ልዩ ድጋፍ ያደረጋችሁ አካላትና የተለያዩ ዕምነት ተከታይ ወገኖቻችን ያደረጋችሁትን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ቤተክርስቲያናችን በልዩ አድናቆት የምትመለከተው ከመሆኑም በላይ ከፍተኛ ምስጋናዋን ታቀርባለች። ወደፊትም በመሰል የአደባባይ በዓላቶቻችን ላይ በጋራ መሥራታችንን አጠናክረን እንድንቀጥል አደራ ትላለች።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት
ጥር ፲፫ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ