ጥር ፫ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
———————-
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
“””””””””””””””””””””

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባህር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም የጌታችን የአምላካችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓልን በማስመልከት “ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ ሰላምን እሻ ተከተላትም” (መዝሙር ፴፬፥፲፫) የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ኀይለ ቃል መነሻ በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት የጥምቀት በዓል ጥንታዊና ሃይማኖታዊ መሰረቱን በጠበቀ መልኩ ሰላማዊ በሆነና በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ ሕዝበ ክርስቲያኑ በኃላፊነት መንፈስ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባው ገልጸዋል።

በዓሉ የቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበ የአገራችን ብሎም የዓለማችን ታላቅ በዓል መሆኑን የገለጹት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በዓሉን በምናከብርበት ጊዜ ሕግን ባከበረ፣ ፍጹም ሃይማኖታዊ ሥርዓትን በጠበቀ፣ በኦርቶዶክሳዊ አለባበስ በተዋበ ሥርዓት በዓለ ጥምቀትን  በማክበር መንፈሳዊ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

በዓለ ጥምቀቱ ዓለም አቀፋዊ እውቅና የተሰጠው በመሆኑን አበክረው የገለጹት ብፁዕነታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ብቻ ሳትሆኑ በሰው ልጆች እኩልነት የምታምኑ   የተለያዩ እምነት ተከታዮች የሆናችሁ ኢትዮጵያን ወገኖች እንደ ሁል ጊዜው እምነታችሁ ባይሆንም “በዓሉ በዓላችን ነው።” እያላችሁ በተለያዩ ጊዜያት አብራችሁን የምታከብሩ፣ ድጋፍ የምታደርጉ ወገኖች በዓሉን ራሳችሁ አክባሪዎች፣ ራሳችሁ የጸጥታው አስተናጋጆች  የሰላም መሪዎች ናችሁ ቅድስት ቤተክርስቲያን በምታስተላልፈው መልዕክት መሰረት በዓሉ በሞቀና በደመቀ መልኩ እንዲከበር የተለመደውን ጥረት ታደርጉ ዘንድ በቅድስት ቤተክርስቲያን ስም ጥሬዬን አስተላልፋለሁ ብለዋል።

የጸጥታ አካላትን በተመለከተ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ባስተላለፉት መልዕክት የጸጥታው አካላት የሀገራችንን ሰላም ባስጠበቀ መንገድ በዓሉን ማክበራችን የሀገራችንን መልካም ነጽታ ማሳየት ይቻል ዘንድ ከማንኛውም ቅሬታ ነፃ በሆነ መንገድ ይህን ካላደረጋችሁ ይህን አናደርግም ከሚል አስተሳሰብ በመራቅ  ሕግን  የማስከበር ሥራችሁን ታከናውኑ ዘንድ  ቤተክርስቲያን መልዕክቷን ታስተላልፋለች ብለዋል።

በሌላ በኩል ጸብ አጫሪዎችን በተመለከተ ባስተላለፉት መልዕክት አሁን አሁን ቅድስት ቤተክርስቲያን እየተጎዳች ያለችው አማኞች ሳይሆኑ ነጠላ የሚለብሱ፣ አማኞች ሳይሆኑ ማተም የሚያደርጉ፣ የቤተክርስቲያን ልጆች መስለው በመካከል ገብተው ችግር ፈጥረው ቤተክርስቲያን ችግር እንደፈጠረች የሚያስመስሉ ስላሉ ተናባችሁ፣ ተዋውቃችሁ፣ በሥነ ሥርዓቱ በዓሉን በልዩ መንገድ እንድናስከብር ቅድስት ቤተክርስቲያን ጥሪዋን ታስተላልፋለች ብለዋል።

ብፁዕነታቸው አክለውም የጥምቀት በዓልን እንዲመራ በጠቅላይ ቤተክህነት  የተሰየመው ዓቢይ ኮሚቴ ከከተማችን አስተዳደርና ከሚመለከታቸው የፀጥታ ኃላፊዎች ጋር  በትላንትናው ዕለት ውይይት ያደረገ መሆኑን ገልፀው በውይይቱ በአንዳንድ አባቶች የተነገሩ ንግግሮችን  ቤተክርስቲያኗ ማውገዝ ይኖርባታል። ይህ ካልሆነ ግን እኛም በትብብር ለመሥራት እንቸገራለን በማለት የገለጹት ሀሳብ  ከጥምቀት በዓል አከባበር ጋር ተያይዞ መነሣቱ አግባብነት የለውም ካሉ በኋላ በተለያዩ ቦታዎች በአባቶች  የሚሰጡትን አስተያየቶች ቤተ ክርስቲያን ለምን በዝምታ አለፈችው የሚል ቅሬታ ቀደም ሲልም  እንዳለ አስታውሰው ቋሚ ሲኖዶስ  በጉዳዩ  ዙሪያ በስፋት ተወያይቶና የሚለውን ብሎ ጉዳዩ በቅዱስ ሲኖዶስ  ምልዓተ ጉባኤ ደረጃ  እንዲታይ  ወደዚያው አስተላልፎታል ብለዋል።

ቤተክርስቲያን ሞትን አታውጅም ትንሣኤን ነው የምታውጀው። ወደ ንስሐ ትጣራለች እንጂ ሞትን አታውጅም  ያሉት ብፁዕነታቸው ጉዳዩን በሰማሁ ጊዜ በጣም ነው ያዘንኩት መግለጫ በግሌ ለመስጠትም ተዘጋጅቼ ነበር ካሉ በኋላ መንገዱን ስናየው ግን መጠላለፊያ እንጂ የጽድቅ ስላልሆነ ነው ዝም ያልነው ብለዋል።

የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስን የአሜሪካ ጉዞን በተመለከተም በሀገረ ስብከታቸው የጥምቀት በዓልን ለማክበር በሀገረ ስብከታቸው ቅዳሴ ቤቱ የሚከበረውን  ቤተክርስቲያን ለመባረክ ታቦት ይዘው ሕጋዊ ደብዳቤ ተጽፎላቸው በህጋዊ መንገድ የተጓዙ መሆኑን ገልጸው የሄዱበትን ሐዋርያዊ ጉዞ አጠናቀው ወደ አገር ቤት በመመለስ መደበኛ ሥራቸውን እንደሚያከናውኑ  አስታውቀዋል።

በመጨረሻም በዓሉ የሰላም፣የደስታ፣የጤናና የበረከት እንዲሆንልን በመመኘት መልዕክታቸውን አጠቃለዋል።