ጥቅምት ፲ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
+++++++++++++++++++
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
“”””””””””””””””””””

ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም የጀመረው የ፵፪ ኛው አጠቃላይ ዓለም አቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ለተከታታይ 5 ቀናት ያደረገውን ውይይት በዛሬው ዕለት አጠናቋል።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በተገኙበት ሲከናወን የቆየው አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ ከመጠናቀቁ በፊት ቃለ ጉባኤውን በማዳመጥ አጽድቋል።

በቃለ ጉባኤው ላይ እንደተጠቀሰው ጉባኤው በቆየባቸው ቀናት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚጠቅሙ ሐሳቦች በመነሳታቸው ለተግባራዊነቱ ሁሉም የራሱን ድርሻ መወጣት አለበት ተብሏል።በተጨማሪም ብፁዕ አቡነ አብርሃም የባሕርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ጉባኤውን የመሩበት ጥበብ አድናቆት ተችሮታል።

ጉባኤው ቅዱስ ፓትርያርኩ እና ብፁዕ ሥራ አስኪያጁ በጉባኤው መክፈቻ ያቀረቡትን ንግግር ሙሉ ለሙሉ እንደተቀበለው በመግለጽ የተለያዩ ነጥቦችን የያዘ አቋም መግለጫ አጽድቋል።

በመጨረሻም ጉባኤው በዘንድሮው የአኅጉረ ስብከቶች ሪፖርት ላይ በአገልግሎት አፈጻጸም እና በበጀት ፈሰስ ከፍተኛ ውጤት ያመጡ አኅጉረ ስብከቶችን በመሸለም ተጠናቋል።