የ ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም የጥምቀት በዓል በሰላም ተከብሮ መዋልን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ ፤

የ ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም የጥምቀት በዓል በሰላም ተከብሮ መዋልን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ ፤
******

ጥር ፲፫ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም
አዲስአበባ ኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየ ዓመቱ ጥር፲ ና ፲፩ቀን የሚከበሩት የከተራና የጥምቀት በዓላት ዘንድሮም በታላቅ ሃይማኖታዊ ሥነሥርዓት ተከብረው ውለዋል።ይህ በቤተክርስቲያናችን የሰላም፣የስምምነት ፣የአንድነትና የመከባበር መገለጫ የሆነው በዓላችን ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መልኩ ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ከበዓሉ ቀድሞ ዐቢይ ኮሚቴ በማቋቋም በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።

የተቋቋመው ዐቢይ ኮሚቴም ንዑሳን ኮሚቴዎቻችን በማደራጀት በየተመደበበት ኮሚቴ ውጤታማ ሥራዎችን አከናውኗል።ይህም በመሆኑ በልዑል እግዚአብሔር ረድኤትና በረከት ስኬታማ በዓል ለማክበር ችለናል።

በተለይም የጠቅላይ ቤተክህነትና የመንግስት የጸጥታ አካላት ያደረጉት የተጣመረ እንቅስቃሴ ለበዓሉ ድምቀትና ማማር እንዲሁም ሰላማዊ በሆነ መልኩ መከበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን ትገነዘባለች።

ለዚህ ስኬታማ የበዓል አከባበር ቤተክርስቲያናችን ከበዓሉ ቀደም ብላ ከካህናት፣ከወጣት የቤተክርስቲያናችን ልጆችና ኦርቶዶክሳዊ ከሆኑ የሚዲያ ተቋማት ጋር ያደረገቻቸው ውጤታማ ውይይቶች በእርግጥም ተነጋግሮ፣ተመካክሮና ተናቦ መስራት ለውጤት የሚያበቃ መሆኑን ያረጋገጡ ናቸው።ይህ አይነቱ የመመካከር ፣የመወያየትና ተናቦ የመስራት ተግባርም ለወደፊቱ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።

ሕዝበ ክርስቲያኑ በተለይም ደግሞ ወጣት ልጆቻችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በበዓል አከባበሩ ዙሪያ በተደጋጋሚ በሚዲያዎች ያስተላለፈቻቸውን መልዕክቶች በመቀበል በዓሉ የቤተክርስቲያያችንን ክብር በሚመጥን መልኩ ተከብሮ እንዲውል በማድረግ ረገድ ያሳያችሁት ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ጨዋነትን የተላበሰ የበዓል አከባበር ሥርዓት የሚደነቅና ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባው ነው።
በዚህም ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የተሰማትን ደስታ ትገልጻለች።

በማዕከል ደረጃ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖትት፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ሚኒስትሮች፣ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት በጃንሜዳ ባህረ ጥምቀት የተከበረው በዓልም እጅግ ባማረና በደመቀ መልኩ ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደርና ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ቅዱስነታቸው እና የክብር እንግዶች በዓሉን ያከበሩበትን ስቴጅና ሳውንድ ሲስተም ከነ ሙሉ ግበዓታቸው እንዲሁም ደረጃቸውን የጠበቁ ድንኳኖችን በማቅረብ ለበዓላችን ድምቀትና ማማር ትልቁን አስተዋጽኦ በማበርከት የሚያስመሰግን ተግባር ፈጽመዋል፤ለዚህም ቤተክርስቲያናችን ልባዊ ምስጋናዋን ታቀርባለች።

በአጠቃላይ በዓላችን በድምቀት ተከብሮ መዋል እንዲችል የደከማችሁ አካላት ሁሉ ልዑል እግዚአብሔር የድካማችሁን ዋጋ እንዲከፍላችሁ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን የዘወትር ጸሎቷ ነው።

በተለይም በዓሉ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መልኩ ተከብሮ መዋል ይችል ዘንድ ሌት ከቀን ስትደክሙ የሰነበታችሁ የጸጥታና ነደህንነት የጋራ ግብረ ሃይል አባላት ድካምና ልፋታችሁ ፍሬ አፍርቶ በዓሉ በሰላም ተከብሮ በመዋሉ ቅድስት ኦሮቶዶሳዊት ቤተክርስቲያናችን የተሰማትን ደስታ ከታላቅ መንፈሳዊ ምስጋና ጋር እየገለጸች እግዚአብሔር አምላክ ሥራችሁን ሁሉ እንዲባርክና የዘወትር ጥበቃው እንዳይለያችሁ አጥብቃ እንደምትጸልይላችሁ ትገልጻለች።

ከበዓሉ በፊት በዓሉን በተመለከተ የቤተክርስቲያናችንን መልዕክት በማስተላለፍ፣በበዓሉ ወቅትም የበዓል አከባበር ሥርዓቱን ለመላው ዓለም በቀጥታና በዜና ሥርጭት በመዘገብ ላይ ለሰነበታችሁ የሚዲያ ተቋማትና ጋዜጠኞችም ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ልባዊ ምስጋናዋን እያቀረበች ሥራችሁ ሁሉ የተሳካና ውጤታማ እንዲሆንላችሁ ልባዊ ምኞቷን ትገልጻለች።

በነገው እለት ወደየ አብያተክርስቲያናቱ የሚገቡት ታቦታትም ልክ እንደዛሬው የበዓል አከባበር ሥነሥርዓት ፍጹም ሰላማዊና ደማቅ በሆነ በመልኩ ይከብሩ ዘንድ ሕዝበ ክርስቲያኑ በተለይም ወጣት ልጆቻችን ታቦታቱ በሰላም ወደየ መንበረ ክብራቸው እንዲመለሱ ቤተክርቲያን ባስተማረቻችሁ የመተሳሰብ፣የመደጋገፍና የመከባበር ሥርዓት መሰረት የሚጠበቅባችሁን ሃይማኖታዊ ግዴታ እንድትወጡ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን መልእክቷን ታስተላልፋለች።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት

ጥር ፲፩ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም
አዲስአበባ ኢትዮጵያ