ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ፳፻ ፲ወ፮ ዓ.ም
“””””””””””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
——————-
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖትን እንኳን ለ2016 ዓ.ም የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በሰላም አደረስዎ ለማለት በተዘጋጀው መርሐ ግብር ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳርና ሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ; ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ;ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ክቡር ሊቀ ትጉሃን ታጋይ ታደለ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጸሐፊ፣ ክቡር ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የየመምሪያውና የድርጅት ኃላፊዎች፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ተገኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ ጸሎተ ወንጌል የደረሰ ሲሆን የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ደቀ መዛሙርት ያሬዳዊ ዜማ አሰምተዋል።
በማስከተልም የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እና የጋሞ ብሔረሰብ ዘማርያን መዝሙር አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ለ2016 ዓ.ም የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት ቅዱስ ፓትርያርኩን የእንኳን አደረስዎ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸውም በዚህች ዕለት ቅዱሳን አባቶቻችን እንዳሉት ‹‹በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ታላቅ ብርሃን ወጣላቸው፤ በቅዱሳን ላይ የሚያድር እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ልዩ ከሆነች ድንግል ሰው ሆኗልና ኑ ይህን ድንቅ እዩ፤ ስለተገለጠልን ምሥጢር ምስጋና አቅርቡ፤ ሰው የማይሆን ሰው ሆኗልና ቃል ተዋሕዷልና ጥንት የሌለው ሥጋ ጥንታዊ ቀዳማዊ ሆነ፣ ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት ዘመን ተቆጠረለት፡፡ የማይታወቅ ተገለጠ፣ የማይታይ ታየ፣ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ በእርግጥ ሰው ሆነ›› እያልን ሐሴት በፍስሐ የጌታችን የልደት በዓል እያከበርን እንገኛን ያሉ ሲሆን፡፡ ስለ ሀገራችን ሰላምና ስለ ቤተክርስቲያናችን አንድነት ቅዱስነታቸው እና ቅዱስ ሲኖዶስ በሚወስናቸው ማናቸውም ውሳኔዎች ለማስፈጸም ያላቸውን ቁርጠኝነት በመግለጽ ቅዱስነታቸውን ለብርሃነ ልደቱ በዓል በሰላም አደረስዎ ብለዋል፡፡
በዝግጅቱ በሊቃውንት ቅኔ የቀረበ ሲሆን ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳርና ሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቅዱስነታቸውን እንኳን ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት አደረስዎ በማለት የመልካም ምኞት መግለጫ አስተላልፈዋል።
ብፁዕ አቡነ አብርሃም “ሰላም በምድር ለሰው ልጅ በጎ ፈቃድ ” በሚል ቅዱስ ቃል መነሻነት ሰብአሰገል ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስጦታ እንዳቀረቡ አስታውሰው በዓሉ ለምድር ሰላም የታወጀበት ታላቅ በዓል ነው ብለዋል። እያንዳንዳችን በተሰለፍንበት ዘርፍ ቤተክርስቲያንን ማገልገል እንድንችል የቅዱስነትዎ ቡራኬና ጸሎት አይለየን ብለዋል። ብፁዕነታቸው በቦሌ ደብረ ሣሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል በልደት በዓል ዋዜማ የተከበረውን በኢትዮጵያዊዉ ጃንደረባ ትውልድ የተሰናዳውን “የአእላፋት ዝማሬ” ልዩና ቤተ ክርስቲያንን የሚመጥን ነው ይህም በቅዱስነትዎ በዘመነ ፕትርክናዎ የተከናወነ በመሆኑ በሚሰጡን መመሪያ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
በክብረ በዓሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ባስተላለፉት መልዕክት እንኳን ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በሰላም አደረሳችሁ በማለት በዓሉን ለማክበር በሥፍራው ለተገኙ ትምህርት ሰጥተዋል።
ቅዱስነታቸው አዳምና ሔዋን ዕፀ በለስን በመብላታቸው ምክንያት በሞተ ሥጋ ላይ ሞተ ነፍስ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነመ እሳት ተፈርዶባቸው 55ዐዐ ዘመን በመከራ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን አዳምና ሔዋን ዕፀ በለሱን ከበሉ በኋላ እግዚአብሔር መሐሪ መሆኑን በመረዳት ንስሐ ገብተው ንስሐቸውን ሲጨርሱ እግዚአብሐር ተስፋ ሰጥቷቸዋል፤ ተስፋቸውም “በሐሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እም ወለተ ወለትከ ” 55ዐዐ ዘመን ሲፈፀም ከልጅ ልጀህ ተወልጄ አድንሃለሁ ብሎ ተስፋ ስለሰጣቸው ይሄን ተስፋ ለመፈፀም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም በመወለዱ ምክንያት አድርገን በዓሉን በታላቅ ድምቀት እያከብርን እንገኛለን ብለዋል።
ነጻ ፈቃድ ቢኖረንም በምርጫችን ልንጠነቀቅ ይገባል ለሀገር ሰላም እና አንድነት ልንሠራ ይገባል ብለዋል።
ቅዱስነታቸው እርሳቸው የተገኙበት በቦሌ ደብረ ሣሌም መድኃኔዓለም ካቴድራል በልደት በዓል ዋዜማ የተከበረውንና በኢትዮጵያዊዉ ጃንደረባ ትውልድ የተሰናዳውን “የአእላፋት ዝማሬ” በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የተሰናዳ ነው ያሉ ሲሆን የሰላም መዝሙር የተዘመረበት ነው ብለዋል።
በመጨረሻም ቅዱስነታቸው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ሰጥተው በጸሎት መርሐ ግብሩ ፍጻሜ አግኝቷል።