“ይህ ዓመት ለሕዝባችን፣ ለሀገራችንና ለዓለማችን ሰላም፣ ደስታና መንፈሳዊ እድገት እንዲያመጣ የዘወትር ምኞቴና ጸሎቴ ነው” ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ ሊቀ ጳጳስ
“ይህ ዓመት ለሕዝባችን፣ ለሀገራችንና ለዓለማችን ሰላም፣ ደስታና መንፈሳዊ እድገት እንዲያመጣ የዘወትር ምኞቴና ጸሎቴ ነው” ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ ሊቀ ጳጳስ
ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ የዩኬ፣ አየርላንድና የሩቅ ምሥራቅ ሀገራት ሊቀ ጳጳስ አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ መልእክት አስተላልፈዋል። የብፁዕነታቸው መልእክት ሙሉ ቃል ከዚህ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
‘‘ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ የአምላክህ የእግዚአብሔር ዓይን ሁልጊዜ በርስዋ ላይ ነው።’’
ኦሪት ዘዳግም ፲፩:፲፪
በዚህ የአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ዕለት ሰፊ በሆነው ምሕረቱ ፣ ጥልቅ በሆነው የአባትነት ፍቅሩ ለሰከንዶች በማይቋረጠው ጥበቃውና እንክብካቤው ሳይለየን ከዘመነ ቅዱስ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ቅዱስ ማቴዎስ አሸጋግሮ ለዚህ ቀን ላደረሰን ሁሉን ቻይ ለሆነው ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋናችንን በፊቱ እናቀርባለን።
በኦሪት ዘዳግም ምዕራፍ 11 ቁጥር 12 ላይ ያሉት አምላካዊ ቃላት አልፋና ኦሜጋ የሆነው አምላችን ልዑል እግዚአብሔር በዘመናት ውስጥ ሁሉ ለሕዝቡ ያለውን ፍቅር የሚያስገነዝብና በተለይም በኦርቶዶክሳዊው ቅዱስ ትውፊት የእግዚአብሔር መግቦትና እንክብካቤ በሕይወታችን ዘመን ሙሉ እንደሚሰራና በፍጹም አባትነቱ እንደሚመራን የምንገነዘብበት ክፍል ነው።
በጥንታውያን ቅዱሳን አባቶቻችን ትምህርትና ሕይወት ባማረውና ባሸበረቀው የቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜያችን ይህ ክፍል እግዚአብሔር ፍጥረታቱን ፈጥሮ የተወ ሳይሆን ይልቁንም ከፍጥረታቱ ያለተለየ የፍጥረታት ሁሉ መጋቢና ጠባቂ መሆኑን እንመለከትበታለን።
አበው እንደተረጎሙትም ‘‘የእግዚአብሔር ዓይን’’ ተብሎ በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ የተጻፈልን ቃል እግዚአብሔር በፍጥረታቱ ላይ የሚያፈሰውን የማያቋርጥ መግቦት፣ ጥበቃ፣ መሪነትና በረከተን የሚያሳይ ነው። ለዚህም ወደር የለሽ መለኮታዊ እንክብካቤ የማያቋርጥ የምስጋና እና የመታዘዝ ሕይወትን በመምራት ራሳችንን በምላሹ ለእርሱ መስጠት ይገባናል።
የ ፳፻፲፯ ዓመተ እግዚእ አዲስ ዓመትን ስንጀምርም፣ ያለፈውን ዓመት እንዴት እንደተጓዝነውና እንዳሳለፍነው በማሰላሰል ልባችንን ለመንፈሳዊ የሕይወት ለውጥና ዕድገት ዝግጁ ማድረግ ይገባናል። ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ የጊዜያችንን አላፊ መሆንና የተሰጠንንም ጊዜ በጥበብ መጥቀም እንዳለብን ካስገነዘበ በኋላ በጥበብ መመላለስ እንደሚገባን ‘‘በልብ ጥበብን እንድማር ቀኝህን እንዲህ አስታውቀን’’ (፹፱:፲፪) በማለት ያስተምረናል።
ጥበብን ማወቅ ማለት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ፣ ሀሳብና መንገድ መጓዟን ፣ ፍትሃዊ መሆንን ፣ ምሕረት ማድረግ መውደድንና ይልቁንም እንደ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በትህትና በምድር ላይ መመላለስና መኖር መቻል ነው።
ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን በእያንዳንዷ ቅጽበት እግዚአብሔርን በማሰብና የእርሱን ከእኛ ጋር መሆኑን ማስተዋል እንደሚገባን ታስተምራለች። የሥርዓተ አምልኮ ማዕከልም ከተሰጠን ከእስትንፋሳችን ጀምሮ ለማያልቀው ከእርሱ ለተቀበልነው ልዩ ልዩ ስጦታዎቹ የማያቋርጥ ምስጋናን ማቅረብና ከእርሱ ያልሆነ ምንም ነገር እንደሌለ ማስገንዘብ ነው።
ቅዱስ ዳዊት ‘‘በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ ፣ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል’’ (፷፬፡፲፩) በማለት እንደዘመረው ፈጣሬ ዓለማት ልዑል እግዚአብሔር ዘመናትን የበረከቱን አክሊል ያቀዳቸዋል። እኛም ልጆቹ በጸሎት፣ በመልካም ሥራና እርሱ ለመምሰል በሚደረግ ክርስቲያናዊ ጉዞ እንድንጓዝ ተጠርተናል።
በመሆኑም አሮጌው አልፎ አዲሱን ዓመት ስንቀበል ቅዱስ ጳውሎስ በ ፪ኛ ቆሮንቶስ መልእክቱ ‘‘ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው’’ (፭:፲፯) በማለት የጻፈልንን ቃል ማሰብና እንደ ቃሉ መኖር ይገባናል።
ይህ ከእግዚአብሔር የተሰጠን አዲስ ዓመት ምድራዊ ለውጥን ብቻ ሳይሆን ይልቁንም መንፈሳዊ የሕይወት ለውጥ እንድናመጣና ዕድገትንም እንድናሳይ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠን አዲስ የንስሐ ጊዜ እንደሆነ እናስብ። ይህ የመንፈሳዊ ሕይወት ለውጥም በቤተክርስቲያናችን ውስጥ በጾም፣ በጸሎትና በቅዱሳት ምሥጢራት አማካኝነት በመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ መሆኑን እናስተውል።
በዚህ አዲስ ዓመት በእነዚህ ከእግዚአብሔር በተሰጡን ቅዱሳት ምሥጢራት አማካኝነት በኃጢአት የጎሰቆለውን አሮጌውን እኛነታችንን ትተን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በማያቋርጥ መንፈሳዊ ዕድገት ውስጥ መገኝት ይገባናል።
የተወደዳችሁ አበው አባቶቻችንና የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ፣
ይህንን አዲስ ዓመት ስንጀምር ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ፣ በጸሎት ሕይወታችን በመበርታት፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባሳየን ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ፍቅር እርስ በእርሳችን በመዋደድ ለቤተክርስቲያናችን ፣ ለሀገራችን ብሎም ለዓለማችን የሰላም ምሳሌዎችና ምንጮች እንሆን ዘንድ በልዑል እግዚአብሔር ስም እማጸናችኋለሁ።
ይህ ዓመት ለሕዝባችን፣ ለሀገራችንና ለዓለማችን ሰላም፣ ደስታ እና መንፈሳዊ ዕድገት እንዲያመጣ የዘወትር ምኞቴና ጸሎቴ ነው።
በዚህ አዲስ ዓመት ዘላለማዊ የሚሆን የሰማይ ቤታችንን ብቻ መመልከት እንችል ዘንድ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነትና እና የቅዱሳን ሁሉ ምልጃ፣ ረድኤትና በረከት ይደርብን ! ከዚህ ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ የእግዚአብሔር በረከቱ፣ ፀጋው፣ ፍቅሩ እና ጥበቃው ከእኛ ጋር ይሁን! አሜን።
‘‘የተስፋ አምላክም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በተስፋ እንድትበዙ በማመናችሁ ደስታና ሰላምን ሁሉ ይሙላባቹሁ ’’ሮሜ ፲፭: ፲፫
አባ ያዕቆብ
የሩቅ ምሥራቅ፣ እንግሊዝ፣ አየርላንድና
አካባቢው ሀገራት አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ