በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መሪ እቅድ ትግበራ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጠ።

በግንቦት ፳፻፲፭ ዓ/ም ርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የጸደቀውንና ለቤተክርስቲያናችን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት መሳለጥ ተጨባጭ ለውጥ ያመጣል ተብሎ የታመነበትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መሪ እቅድ በሠፊው የሚተነትንና የሚያስረዳ የአንድ ቀን ሥልጠና የመንበረ ፖትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት አስፈፃሚ አካላት ለሆኑት ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ የመምሪያና ድርጅት ኃላፊዎችና ለምክትል ኃላፊዎች ተሰጠ።

የሰኔ ማርያም በዓለ ንግሥ ቅዱስ ፓትርያርክ በተገኙበት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በታላቅ ድምቀት ተከበረ።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት እና ብፁዕ አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ዛሬ ሰኔ ፳፩ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም የሰኔ ማርያም በዓለ ንግሥ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በድምቀት ተከበረ ።

የምሥራቅ አውስትራሊያና ኒውዚላንድ ሀገረ ስብከት በጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው አብያተክርስቲያናት ርዳታ ሰጠ።

በኢ.ኦ.ተ.ቤ. የምሥራቅ አውስትራሊያ እና ኒውዚላንድ ሀገረ ስብከት በጦርነትና በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት ለደረሰባቸው አብያተ ክርስቲያናት ማቋቋሚያ የሚሆን የ 2,091,000.00(ሁለት ሚሊየን ዘጠና አንድ ሺ) እርዳታ አበረከተ።

በሰሜን አሜሪካን የሚገኘው ዳግማዊ ደብረ ሊባኖስ ቅዱስ ያሬድና አቡነ ፊሊጶስ ገዳምና የአብነት ትምህርት ቤት ከስልሳ በላይ ታዳጊ ወጣቶችን በመንፈሳዊ የትምህርት ዘርፍ እያሰለጠነ ነው።

በሰሜን አሜሪካን ቨርጂኒያ ግዛት ኪንግ ጆርጅ ካውንቲ የሚገኘው ዳግማዊ ደብረ ሊባኖስ ቅዱስ ያሬድና አቡነ ፊሊጶስ ገዳም አንድ መቶ ሃያ ተማሪዎችን በሁለት ዙር በመቀበል በልዩልዩ መንፈሳዊ ትምህርት ዘርፎች ማስተማር ጀመረ።

የ፳፻ ፲ወ፭ ዓ/ም የስብከተ ወንጌል እና የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ የጋራ የአገልግሎት ሥምሪት ሥልጠና ተከናወነ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፖትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያና የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ በጋራ የሚያስተባብሩት በስብከተ ወንጌል ማስፋፋትና በሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አደረጃጀት ዙሪያ በ፵፰ አህጉረ ስብከት ሥልጠና ለመሥጠት ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ።

ወቅታዊ መልዕክት

በአንዳንድ ማኅበራዊ ገጾች እየተዘዋወረ የሚገኘው እና በብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ስም ተፈርሞ እንደወጣ በማስመሰል የተለቀቀው ከዚህ በታች የሚታየው ደብዳቤ ፍጹም የሐሰትና ሆን ተብሎ ተቀነባብሮ በፎርጅድ ተሰርቶ የተለጠፈ መሆኑን እንገልጻለን።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት።
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
ሰኔ ፲፬ቀን ፳፻ ፲ወ፭ዓ.ም

በክልል ትግራይ ካሉ ብፁዓን አባቶች ጋር የተፈጠረውን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት እየተሠራ እንደሆነ የሰላም ልዑኩ ገለጸ ።

ሰኔ ፯ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ዓ.ም
*****
አዲስ አበባ -ኢትዮጵያ
“””””””””””””””””””””

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይነበባል

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ
አምላክ አሜን !!!

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና የስምምነት ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የካቲት 7 ቀን 2015 ዓ.ም በቅዱስነታቸው ፊርማ ባወጣው ደብዳቤ በትግራይ ክልል የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ በካህናት ፣ በምእመናን ፣ በገዳማትና በአድባራት ላይ ስለደረሰው ጉዳት የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን በይፋ መግለጹ ይታወሳል።

በግንቦት ወር ባካሄደው የርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤም በክልል ትግራይ የሚገኙ አባቶቻችን የሚያነሱትን ቅሬታ በተመለከተ ጉዳዩ በውይይትና በህግ የሚፈታበት መንገድ እንዲፈጠር ቀደም ሲል በቅዱስ ሲኖዶስ የተሰየመው ኮሚቴ ሥራውን እንዲቀጥል መመሪያ ሰጥቶ ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ውሳኔ አስተላልፏል።

የተቋቋመው ኮሚቴም ችግሩ በሰላማዊ መንገድና በስምምነት መቋጨት የሚችልበትን አቅጣጫ በመቀየስ በርካታ የቅድመ ውይይት ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።ወደፊትም የቅዱስ ሲኖዶስን መመሪያ በመቀበል ችግሩ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በተከተለ አግባብ መፍትሔ እንዲያገኝ ለማድረግ የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ ደፋ ቀና እያለ ይገኛል።

በክልል ትግራይ የሚገኙ ብፁዓን አባቶቻችን የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ሁሉ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በተከተለ አግባብ ለመፍታት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን የምታደርገውን የእናትነት እንቅስቃሴ በማዛባት ልዩነት እንዲሰፋና የቤተክርስቲያናችን ተቋማዊ አንድነት እንዲናጋ ሌት ተቀን የሚጥሩ አንዳንድ የሚዲያ ተቋማትም ችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሔ እንዳያገኝ ሆን ብለው እየሠሩ እንደሚገኙ እንገነዘባለን።

ይሁንና ችግሩ የሚፈታው በእልህና በቁጣ ልዩነትን በማስፋትና በመራራቅ ሳይሆን በሰከነ መንገድ በሰለጠነ አስተሳሰብና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን መሠረት ባደረገ በግልጽ ውይይት መሆኑን በመገንዘብ የችግሩ መነሻዎችን አሁን ያሉበትን ደረጃና ወደፊት ሊደረግ የሚገባ የሚባሉ ነጥቦችን በመለየት በውይይት መፍታትና በመጨረሻ ጉዳዩን በእርቀ ሰላም ማጠቃለል እንደሚገባም ኮሚቴው በጽኑ ያምናል።

ስለሆነም በክልል ትግራይ የሚገኙ ብፁዓን አባቶቻችን ቀደምት አባቶቻችን ለሃይማኖታቸው አንድነትና መስፋፋት እንዲሁም ለቀኖና ቤተ ክርስቲያን መጠበቅ የከፈሉትን መስዋዕትነት መሠረት በማድረግ የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችሁ አንድነትና ሉዓላዊነት በጽናት በመቆም ተፈጠሩ የሚባሉ ችግሮችን ሁሉ በዝርዝር ለማቅረብ ለውይይት ዝግጁ እንድትሆኑ መልእክታችንን እያስተላለፍን የምታቀርቧቸውን የውይይት ነጥቦች መሠረት በማድረግ ችግሮቹን በስምምነት ለመፍታት ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ዝግጁ መሆኗን እንወዳለን።

በዚህም የውይይትና የሰላም መልእክታችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ያስተላለፈችውን ጥሪ በመቀበል በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውይይትና ለስምምነት ዝግጁ እንድትሆኑ ጥሪያችንን እያስተላለፍን በቅርብ ቀናት ውስጥ የሰላም ልዑኩ ለውይይት ወደ ክልል ትግራይ መቀሌ ከተማ ስለሚጓዝ በጋራ በምናደርጋቸው ቦታና ጊዜ የውይይትና የስምምነት ጉባኤ የሚደረግ ይሆናል።

የፌዴራል መንግሥትና የክልል ትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርም ችግሩ በሰላማዊ መንገድና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በጠበቀ መልኩ መፍትሔ ያገኝ ዘንድ የሚደረገውን ጥረት ሁሉ በመደገፍና ለውይይቱ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግልን በዚሁ አጋጣሚ መልእክታችንን ለማስተላለፍ እንወዳለን።

አምላካችን እግዚአብሔር ኢትዮጵያ ሀገራችንንና ሕዝባችንን ይባርክ !

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የሰላምና የስምምነት ኮሚቴ

ሰኔ 5 ቀን 2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

 

በትግራይ ክልል ከሚገኙ አባቶች ጋር ውይይት ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተጠናቀቀ።

ሰኔ ፫ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም
“”””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
******

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በግንቦት ወር ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም ባካሔደው የርክበ ካህናት ጉባኤ በትግራይ ክልል ከሚገኙ አባቶች ጋር የሚደረገው ውይይት ቀደም ሲል በቋሚ ሲኖዶስ በተሰየመው የልዑካን ቡድን አማካኝነት በአስቸኳይ እንዲቀጥል መወሰኑ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ ኮሚቴው ውይይቱን በተሳካ ሁኔታ ለማካሔድ የሚያስችለውን በእቅድ ላይ የተመሰረተ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ሲያከናውን የቆየ ሲሆን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ውይይቱ በተሳካ ሆኔታ መካሔድ የሚችልበትን ሁኔታ እንዲያመቻች በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በተጻፈ ደብዳቤ ጥያቄውን አቅርቧል።የልዑካን ቡድኑ አባላትም ከቅዱስ ፓትርያርኩ የተጻፈውን ደብዳቤ በአካል በመገኘት ለክልሉ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት በማቅረብ ከሚመለከታቸው የክልሉ የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር የክልሉ ጊዚያዊ መንግስት ለውይይቱ መሳካት በሚያደርገው ድጋፍ ዙሪያ ውይይት በማድረግ ተመልሷል።

ስለሆነም ለክልሉ መንግስት በቀረበው ጥያቄ መሰረት ሁለቱም አካላት በሚያመቻቹት ጊዜና ቦታ ውይይቱ የሚካሔድ ይሆናል። በዚህም መሰረት የጠቅላይ ቤተክህነት ልዑካን ቡድን ውይይቱን ውጤታማ ለማድረግ ይቻል ዘንድ እስከ አሁን ያከናወናቸውን ተግባራትና ወደፊት ውይይቱን ስኬታማ በሆነ መንገድ ማካሔድ በሚችልበት ሁኔታ ዙሪያ ሰኞ ሰኔ ፭ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ይፋዊ መግለጫ ይሰጣል።መግለጫውን ተከትሎም ጉዳዩ በቀኖና ቤተክርስቲያን መሰረት የመጨረሻ እልባት እንዲያገኝ በፍጥነት ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በመግባት በሒደቱ የሚመዘገቡ ለውጦችን ሁሉ በመገናኛ ብዙሃን የሚያሳውቅ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
ሕዝብ ግንኙነት መምሪያ
ሰኔ ፫ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በተገኙበ በአቡዳቢ ደብረ ሰላም መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያንበዓለ ጰራቅሊጦስ ተከበረ።

በዓለ ጰራቅሊጦስ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በአቡዳቢ ደብረ ሰላም መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ውሏል።

ወቅታዊ መልዕክት ለምዕመናን

የደብረ ኤልያስ ብሔረ ብፁዓን መልክዓ ሥላሴ አንድነት ገዳምን በተመለከተ በበርካታ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችና የመገናኛ አውታሮች ልዩ ልዩ ዘገባዎች እየተላለፉ ይገኛሉ።

ይህን ተከትሎም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ገዳማት አስተዳደር መምሪያ ከሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት ጋር በመገናኘት ተፈጸመ የተባለውን ችግር በተመለከተ በዝርዝር የማጣራት ሥራ እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤትም በማዕከል ደረጃ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ላይ ይገኛል።

ስለሆነም ዝርዝር ሁኔታው በሚገባ ተጣርቶ የተደረሰበት የማጣራት ውጤት እውነታውን በሚገባ በሚያሳይ መልኩ በቤተክርስቲያናችን ማዕከላዊ አስተዳደር የሚገለጽ ይሆናል።

በሌላ በኩል በአርሲ ሀገረ ስብከት በጢዮ ወረዳ በጨፌ ሚሶማ ቀበሌ ገበሬ ማኀበር በዴራ አማኑኤል አጥቢያ ቤተክርስቲያን ግንቦት ፳ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም ምሽት ላይ በኦርቶዶክሳውያን ላይ ደረሰ ተብሎ በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች የተገለጸውን ጥቃት በተመለከተ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን የተሰማትን ጥልቅ ሐዘን እየገለጸች በሀገረ ስብከቱ በኩል ተጣርቶ በሚቀርቀው መረጃ መሰረት ጉዳዩን በህግ አግባብ የምትከታተለው መሆኑን ትገልጻለች። ልዑል እግዚአብሔር የሟች ወገኖቻችንን ነፍስ በአብርሃም፣በይስሐቅና በያዕቆብ ዘንድ እንዲያኖርልንም ቅድስት ቤተክርስቲያናችን የዘወትር ጸሎቷ ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት

አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
ግንቦት ፳፬ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም