የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለትግራይ ክልል የ20 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገች

(ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለትግራይ ክልል የ፳ ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገች፡፡በድጋፍ ርክክብ መርሐ ግብሩ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት እና ልዑካን ቡድኑ ተገኝተዋል፡፡

በቅዱስ ፓትርያርኩ የሚመራ ልዑካን ቡድን ወደ ክልል ትግራይ ርዕሰ ከተማ መቐለ ተጓዘ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለክልል ትግራይ የሰብዐዊ ድጋፍ እንዲደረግና ቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በትግራይ ክልል ከሚገኙ አባቶች ጋር ውይይት እንዲደረጉ ውሳኔ አስተላልፏል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የማኅበራት ምዝገባና ክትትል መምሪያ ቀጣዩን የሥራ አተገባበር አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያ የማኅበራት ምዝገባና ክትትል መምሪያ በጥቅምት ወር ፳፻፲፭ ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ ዕውቅና ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ የውስጥ አሠራሩን ሲያመቻች የቆየ መሆኑን የሕግ ባለሙያው አቶ አያሌው ቢታኒ ሐምሌ ፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

የሕግ ባለሙያው አቶ አያሌው ቢታኒ ከዚሁ ጋር አያይዘው እንዳብራሩት የማኅበራት ምዝገባና ክትትል መምሪያ የመተዳደሪያ ደንብና የአፈጻጸም መመሪያ ተዘጋጅቶለታል።
ለተመዝጋቢ ማኅበራትም ሞዴል የሚሆን ቅጽ ተዘጋጅቷል ያሉት የሕግ ባለሙያው ወደ ምዝገባ የሚገቡ ማኅበራት የጠቅላላ አባላቱ ቁጥር ሰባት መቶ ሀምሣ እና ከዚያ በላይ የሆኑ ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታይ መሆናቸው በማስረጃ የተረጋገጠላቸው፣የንስሐ አባት የያዙ፣ በትምህርተ ሃይማኖት በቂ ዕውቀት ያላቸው ይሆናሉ ብለዋል።

አቶ አያሌው ቢታኒ በሰጡት ማብራሪያ አክለው እንደገለጹትም በማኅበራት ምዝገባና ክትትል መምሪያ ከሚካተቱት የማኅበራት ዘርፎች ከስምንት ያላነሱ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የማኅበራት አንድነት፣የሙያ ማኅበራት፣የበጎ አድራጎት ማኅበራት፣የሐዋርያት ማኅበራት ፣መንፈሳዊ አስጎብኚ ማኅበራት ይገኙባቸዋል።

ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የደቡብ ትግራይ ማይጨው እና ደቡብ ምሥራቅ ትግራይ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የማኅበራት ምዝገባና ክትትል መምሪያ የበላይ ሐላፊ ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት አባታዊ መልእክት የማኅበራት ምዝገባና ክትትል መምሪያ ዋና ዓላማው ልዩ ልዩ ፈተና በበዛበት በዚህ ዘመን ምእመናን አንድነታቸውን እያጠናከሩ ባንድ ላይ በመቆም ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ እንዲረዳቸው ታስቦ ሲሆን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንንም ባንድ ላይ ሆነን ለማሻገር እንድንችል ነው ብለዋል።

ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ክፍሎች ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ደቀመዛሙርትን አስመረቀ

ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ በሥሩ ባሉ የተለያዩ ኮሌጆችና በተለያዩ የትምህርት ክፍሎች በመደበኛ፣ በተከታታይ፣ በርቀትና በልዩ የካህናት ሥልጠና ትምህርታቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁ ፫፻፸፮ ደቀመዛሙርትን በድኅረ ምረቃ፣ በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በዲፕሎማና በሰርተፊኬት ማዕረግ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የኒው ዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የጉራጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የዩኒቨርሲቲው የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ፣ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳት፣ ክቡር ሊቀ አእላፍ በላይ መኮንን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም በክብር ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የተመራቂ ቤተሰቦች በተገኙበት በደማቅ ሥነ ሥርዓት አስመረቀ።

ቅዱስ ፓትርያርኩ አልሾምም ወደ ትግራይም ፤ አልሔድም አላሉም

ሰኔ ፳፱ ቀን ፳፻ ፲ ወ፭ ዓ.ም
“”””””””””””””””””””””””””
አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ
******

በአንዳንድ ማኅበራዊ ሜዲያዎች ቅዱስ ፓትርያርኩ በቅዱስ ሲኖዶስ “የተመረጡትን መነኮሳት አልሾምም፤ ወደ ትግራይም አልሔድም”ብለዋል ተብሎ የተሰርጭው ዜና ፍጹም ሐሰት ነው። የተመረጡትን አባቶችንም አልሾምም አላሉም። በተያዘው መርሐ ግብር መሠረትም ወደ ትግራይ ይጓዛሉ።

እንዲህ ዓይነቱ ሆን ተብሎ የሚሰራጭ የሐሰት ዘገባ ፤ የእርቅ ሂደቱን የማደናቀፍ እና የቅዱስ ፓትርያርኩን ስም በሐስት የማጠልሽት የተለመደና ቀጣይ የሐሰተኞችና ስም አጥፊዎች ዘመቻ አካል መሆኑን እየገለጽን ይህን አይነቱን የሐሰትና የፈጠራ ወሬ በቅድስት እርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን ላይ የሚነዙ አካላትም ከዚህ ደርጊታቸው እንዲታቀቡ ቅድስት ቤተክርስቲያን በጥብቅ ታሳስባለች።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ

አዲስ በሚሾሙት ኤጲስቆጶሳት የአመራረጥ አካሄድ ዙሪያ በአስመራጭ ኮሚቴ አባላት ብፁዓን አባቶች ማብራሪያ ተሰጠ።

ሰኔ ፳፱ ቀን ፳፻፲፭ ዓ/ም አዲስ አበባ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የግንቦት ርክበ ካህናት ምልአተ ጉባዔ ለ፯ የኦሮሚያ እና ለ፪ የደቡብ ክልል አህጉረ ስብከት በኤጲስቆጶስነት የሚሾሙ ቆሞሳትን መልምለው ለምልአተ ጉባዔ እንዲያቀርቡ የተመረጡት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ባከናወኑት የምልመላ ሂደት ዙሪያ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ተሰጥተዋል።

በተሰጠው ማብራሪያ መሠረት በእጩነት የቀረቡት ቆሞሳት በመንፈሳዊ ትምህርት፣ በአገልግሎት፣ በግብረገብነትና የሚመደቡበትን ሀገረ ስብከት ምእመናን በቋንቋቸው በማስተማር ረገድ በቂ ዝግጅት ያላቸው ስለመሆናቸው ጥቆማውን ካቀረቡት አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና ከቀረቡት ተያያዥ ሠነዶችና የሕይወት ታሪኮች መረዳት መቻላቸውንና ይህንንም ለምልአተ ጉባኤ ማቅረባቸውን በዚህም መሠረት ድምጽ ተሰጥቶ ተሿሚዎች መለየታቸውን አብራርተዋል። ምንም እንኳ ለምልአተ ጉባኤ የቀረቡት ቆሞሳት ቁጥር ፲፰ ቢሆኑም ቀድሞ በጥቆማ የቀረቡት አባቶች ቁጥር ፸፭ እንደነበሩ በኮሚቴው ጸሐፊ በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ተገልጿል።

ጥቆማው፣ ግምገማውና ምርጫው ምእመናንና ካህናት አልተሳተፉበትም በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም:- ምንም እንኳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የካህናት እና የምእመናን የጋራ የአገልግሎት ቦታ የሰማያዊት ኢየሩሳሌም አምሳል ስለመሆኗ ሁሉም የሚያምነው እውነት እንደሆነ ሁሉ ቤተክርስቲያናችን ከራሷ ልጆች ሊቃነ ጳጳሳትን መሾም ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ የምርጫ ሂደት የሚካሄደው በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ብቻ በመሆኑ የዛሬውም ከቀድሞ አሠራር የተለየ አይደለም ቢሆንም ግን የካህናትንና የምእመናንን ይሁንታ ለማወቅ በተለያዩ መንገዶች ተጠቋሚዎቹ አባቶች ካገለገሉባቸው አህጉረ ስብከት እና አጥቢያዎች መረጃ ጠይቀናል ከዚህም ባሻገር ሊቃውንትንና ምእመናንን ለማሳተፍ የተሠራ ሥርዓት ሳይሠራ ወደማሳተፍ ቢገባ ችግር ሊያመጣ ይችላል የሚል ስጋት ስለመጣ በነበረው የአመራረጥ ልማድ ተከናውኗል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ጥር ፲፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓ/ም ከቀኖና ቤተክርስቲያን ውጪ ከተሾሙ አባቶች መካከል የተወሰኑት ለምን ተካተቱ በሚል ለተነሳው ጥያቄም ምላሽ የሰጡት አበው ሊቃነ ጳጳሳት አስቀድሞ የቤተክርስቲያናችንን ሰላምና መዋቅራዊ አንድነት ለመጠበቅ በተደረገው የሰላም ስምምነት መሠረት ውግዘቱ ሲነሣ ፍጹም ሰላም ስለመፈጠሩ ቅዱስ ሲኖዶስ እምነት ስላደረበት ለሲመቱ ብቁ መሆናቸው የታመነባቸው ለንስሐ የበቁ አባቶችን መግፋት አስፈላጊ ባለመሆኑ የተወሰኑት አባቶች በእጩነት ቀርበው በቅዱስ ሲኖዶስ የታመነባቸው መመረጣቸውን እንዲሁም ቀድሞ በችግሩ ወቅት በነበረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በተደረገው ውይይት በጓዳ ለመግባት የተደረገውን ሙከራ አወገዘ እንጂ በተደረገው ጥናት ያለእውቀት በተለያየ ወቅታዊ ስብከትና ጫና ተታለው የገቡ መኖራቸው በመረጋገጡ ሊመረጡ ችለዋል ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሲያካሂድ የነበረውን አስቸኳይ ስብሰባ በማጠናቀቅ የተሰጠ መግለጫ

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የሚመራ የልዑካን ቡድን ሐምሌ ፫ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም ወደትግራይ ርዕሰ ከተማ መቐለ ይጓዛል።

ሰኔ ፳፰ቀን ፳፻ ፲ ወ፭ ዓ.ም
*****
አዲስ አበባ-ኢትዮጵያ
******

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ ባስ ተላለፈው ውሳኔ መሰረት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የሚመራ የልዑካን ቡድን ሐምሌ ፫ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ .ም ወደ ክልል ትግራይ ርዕሰ ከተማ መቐለ ይጓዛል።

ልዑካን ቡድኑ ወደ መቐለ የሚጓዘው በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔ መሰረት ለትግራይ ክልል እንዲሰጥ የተወሰነውን ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስና በትግራይ ከሚገኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በሰላም ጉዳዮች ዙሪያ ለመነጋገር መሆኑ ታውቋል።ይህንን በተመለከተም ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት ለትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት የተላከው ደብዳቤ ለፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤት ዛሬ ማለዳ እንዲደርስ ተደርጓል።