የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ልጅ ያሬድ በተባለው ግለሰብ እና ተባባሪዎቹ ላይ ክስ እንዲመሠረት ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ጥያቄ አቀረበች።

ነሐሴ ፳፱ ቀን ፲ወ፭ ዓ.ም
“”””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
******

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ልጅ ያሬድ በተባለውን ግለሰብ እና በተባባሪዎቹ ላይ ክስ እንዲመሠረት ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ በላከችው ደብዳቤ ጠይቃለች።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ባቀረበችው አቤቱታ ከዚህ ቀደም በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምሮ ፣ በሃይማኖት አባቶቿ ፣ በምዕመናኗ እና የአምልኮ ቦታዎቿን ባንቋሸሹ እንዲሁም የሐሰተኛ ንግግር ባስተላለፉት በነፓስተር ዮናታን አክሊሉ ፣ በነቢይ ኢዩ ጩፋ ፣ በአዲስ ኪዳን ካህናት ቤተ ክርስቲያን እና በክራይስት አርሚ ኢንተርናሽናል ቤተ ክርስቲያን ላይ ላቀረበችው አቤቱታ ውጤት በመጠባበቅ ላይ ሳለች ይን የመሰለ ድፍረት የተሞላበት ድርጊት እንደገጠማት ገልጻለች።

በዚህ በግለሰቡ እና ተባባሪዎቹ ድፍረት የተሞላበት ድርጊት በበርካታ ኦርቶዶክሳዊያንና ኢትዮጵያውያን ላይ ከፍተኛ ቁጣን በመቀስቀሱን እና ከፍትህ አደባባይ ፍርድን ለማግኘት ይቻል ዘንድ ይሔን አቤቱታ ማቅረቧን በጻፈችው ደብዳቤ ገልጻለች።

የተከሳሹ ድርጊት በዋናነት የቤተ ክርስቲያኗን መልካም ስም የሚያጎድፍ ድርጊት ከመሆኑም በላይለቤተ ክርስቲያን ያለውን ጥላቻ በድፍረት በመግለጽ ሰዎችን ለአመጽ እና ብጥብጥ የሚያነሳሳ በመሆኑ ፤ የቤተክርስቲያንን የአምልኮ ቦታ ያራከሰ በመሆኑ ፤ የምዕመናኑን ስሜት የሚነካ ፣ በሚያዋርድ መልኩ የተፈጸመ በመሆኑ በግለሰቡ እና በተባባሪዎቹም ላይ ጭምር ፖሊስ ተገቢውን ምርመራ በማድረግ ክስ በመመስረት ለአቃቤ ሕግም እንዲልክ ጠይቃለች።

 

“ቤተክርስቲያን የተፈተነችበት ሥርዓቷን እና ልጆችዋን ያጣችበት ጊዜ ስለሆነ ለሀገራችን እና ለቤተ ክርስቲያናችን ሰላም እንዲመጣ የጷጉሜን ፮ቀናት ወደ እግዚአብሔር እንጸልይ።” ብፁዕ አቡነ አብርሃም

ነሐሴ ፳፱ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም
******
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
“””””””””””””””””””””

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የጷጉሜን ፮ ቀናት ጸሎተ ምህላ እንዲኖር አወጀ።

ዛሬ ነሐሴ ፳፱ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም በብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና በአቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የባህርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በተሰጠው መግለጫ መሰረት የጷጉሜን ወር ፮ ቀናት መላው ኦርቶዶክሳዊ በጸሎት እና በምህላ እንዲያሳልፍ መታወጁን ነው የገለጹት።

በመግለጫውም ዘመኑ ከደስታ እና የምስራች ይልቅ ሀዘንን የምንሰማበት ዘመን ስለሆነ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን የተቸገሩትን የተራቡትን ፣ የተፈናቀሉትን እና የተጎዱትን እያሰቡ በጾም እና በጸሎት እንዲያሳልፉ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ 13ተኛ ወር በሆነችው ወርሐ ጷጉሜ እለተ ምጽዓትን የምናስብበት ፤ ሠማይ የሚከፈትበት ፤ ጸሎት የሚሰማበት ሚስጥራዊ የሆነች ወር ነችና የበደሉንን ይቅር ብለን በንጹሕ ልቦና የቻልን ጾመን ያልቻልን በጸሎት እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት እና የምንለምንበት ወር ሊሆን ይገባል ሲሉ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ገልጸዋል።

ብፁዕነታቸው የቤተ ክርስቲያን በዓላት ሲደርሱ ከሥርዓቷ እና ከአስተምሮዋ ውጪ በ ሆነ መልኩ የተለያዩ አካላት የዳንኪራ ጥሪ በማዘጋጀት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አግባብነት የሌለው መሆኑን እና ምዕመናንም ከዚህ እንቅስቃሴ እራሳቸውን ሊያርቁ ይገባል ነው ያሉት።

የማትደፈረዋን እና የማትነካዋን ቤተክርስቲያን የሚነኩ ሰዎች በዝተዋል ፤ ቀጣዩ ዓመትም ኢትዮጵያውያን በሰላም በፍቅር የምንኖርበት የሚራቡ የሚፈናቀሉ የሚያዝኑ ሰዎች እንዳይኖሩ ሁሉም ምዕመን ጠዋት ኪዳን ከሰዓት በሠርክ ጸሎት በየአብያተ ክርስቲያን በመሄድ ያልቻለም በየቤቱ ሊጸልይ ይገባል ብለዋል።

ልጅ ያሬድ የተባለውን ግለሰብ በህግ ለመጠየቅ የሚያስችል ሥራ እየተሰራ ነው።

ነሐሴ ፳፮ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም
*******
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ
******

ባለፉት ቀናት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ውስጥ በመግባት ከእምነቷ ውጭ የሆነ መዝሙር የዘመረች ወጣት የፈጸመችው ተግባር ጥፋት መሆኑን አምና በፈጸመችው ጥፋት በመጸጸት በቅድስት ቤተ ክርሰቲያን አውደ ምህረት ተገኝታ ይቅርታ መጠየቋን ተከትሎ ልጅ ያሬድ የተባለ ግለሰብ እንኳን የኃይማኖት ሀገር በሆነችው ኢትዮጵያ ቀርቶ እምነት የለሽ በሚባሉት ሀገራት የማይደረግ የድፍረት ስድብና አጋንታዊ የሆነ ጸያፍ ቃላትን በመጠቀም በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ በማህበራዊ ድህረ ገጹ ላይ በተደጋጋሚ ያስተላለፈውን መልዕክት ተመልክተነዋል።

በዚህ ድፍረት የተሞላበት ድርጊትም በርካታ ኦርቶዶክሳውያን አዝነዋል፣አልቅሰዋል፣ በድርጊቱ ክፉኛ በመበሳጨትም ከፍትህ አደባባይ ፍርድ እንደሚጠብቁ በተለያየ መልኩ እያሳወቁ ናቸው።

ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን መስቀል ሁሌ መሸከም የየዕለት ተግባሯ ቢሆንም ከ፷ሚሊዮን በላይ ተከታይ ያላትንና ላለፉት ሁለት ሺህ ዘመናት ሀገርን በፍቅርና በስነምግባር ጥላ ሥር ሰብስባ ያኖረች ቤተ ክርስቲያን መሆንዋ እየታወቀ በእንዲህ አይነት በወረዳና ተሰምቶ በማያውቅ ድፍረት ቤተክርስቲያንን በመስደብ ሕዝበክርስቲያኑን ለማሳዘን መሞከር እጅግ አደገኛ ተግባር ነው።

ቤተክርስቲያንም ይህን ጸያፍ ተግባር የፈጸመና የተሳደበን ግለሰብ በዝምታ ማለፍ ስለማይገባት ጉዳዩን በህግ መምርያ በኩል በመከታተል ተገቢውን ሁሉ የምታደርግ መሆኑን ከወዲሁ እየገለጸች በህግ መምሪያችንና በህግ ባለሙያዎቻችን አማካኝነት አስፈላጊውን ሁሉ እስክታደርግ ድረስ ምዕመናን ከቅድስት ቤተክርስቲያን የተማራችሁትን ትዕግስትና ትህትናን መሰረት ባደረገ አግባብ በፍጹም ክርስቲያናዊ ጨዋነት እንድትጠብቁና በጉዳዩ ዙሪያ ከጸጥታ ከአካላት ጋር በትብብርና በአንድነት በመጠቆም እንድትተባሩ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ጥሪዋን ታስተላልፋለች።