በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብር በመካሔድ ላይ ነው

ጥር ፳፫ ቀን ፳፻ ፲ወ ፭ ዓ.ም
*******
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
“””””””””””””””””””””
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ ጥር፲፰ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም ባካሔደው ስብሰባ የሰጠውን ዝርዝር ውሳኔ አፈጻጸምን በተመለከተለ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የየመምሪያው ኃላፊዎች፣የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎችና የየአህጉረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆች ያተሳተፉበት የውይይት መርሐ ግብር በጠቅላይ ቤተክህነት ጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ በመካሔድ ላይ ነው።

በመርሐ ግብሩ ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ውሳኔን በተመለከተ፣ተከናወነ የተባለውን ኢ-ሕጋዊ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመትን በተመለከተ፣የተጣሰውን ኢ-ቀኖናዊ የቤተክርስቲያን እና አስተዳደራዊ ጥሰቶችን በተመለከተ፣የተከናወነው ጥሰት ከዓለም አቀፍ አበብያተ ክርስቲያናት ተሞክሮ አንጻር ፣በቀጣይ በሁሉም የቤተክርስቲያን መዋቅሮች ምን መሰራት ይገባናል የሚሉ ሐሳቦች ውይይት ይደረግባቸዋል።

ጉባኤው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የመክፈቻ ጸሎትና የመግቢያ መልዕክት ተከፍቷል፤ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም ብፁፅ አቡነ ጴጥሮስ ዶ/ር የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒዩወርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስም የስብሰባውን አስፈላጊነት በተመለከተ መልዕክት አስተላልፈዋል።ጉባኤው ከፍ ሲል በተጠቀሱት ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሙሉ ቀን ውይይት በማድረግ የጋራ የአቋም መግለጫ በማውጣት ይጠናቀቃል።