አሥሩን ነጥቦች ያለመሸራረፍ ለመተግበር እነ አቡነ ሳዊሮስ ተስማሙ።ወቅታዊ መግለጫ

******
የካቲት ፲፩ቀን፳፻ ፲ወ፭ዓ.ም
“””””””””””””””””””””””””””
አዲስአበባ -ኢትዮጵያ
******

ጥር ፰ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም ክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ በተገኙበት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሦስት ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና እነ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በተገኙበት በተደረገው ውይይት ፲ የስምምነት ነጥቦች ተቀምጠው በነጥቦቹ ላይ የጋራ መግባባት ከተደረሰ በኋላ የጋራ መግለጫ በመስጠት ስምምነቱ መጽደቁ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም ስምምነቱን ሙሉ ለማድረግና ዕርቁን ተቋማዊ ለማድረግ በማሰብ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነ አቡነ ሳዊሮስን በመያዝ ወደ መንበረ ፓትርያርክ በማምጣት ከቅዱስነታቸው ጋር እንዲገናኙ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ዛሬ የካቲት ፲፩ ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን በመወከል በስምምነቱ ላይ የተሳተፉት ብፁዓን አባቶችና እነ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ ተገናኝተው ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኋላ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት የተደረሰውን ስምምነት በምንም መልኩ መጣስ እንደሌለበት በመተማመን በዛሬው ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫውም “በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ክቡር ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር አብይ አሕመድ በተገኙበት የካቲት ፰ቀን ፳፻ ፲ወ፭ ዓ/ም በተደረገው ውይይት የተስማማንባቸውን (፲) ዐሥር ነጥቦች ያለመሸራረፍ ለመፈጸም እንዲሁም ቀጣዩን ተግባር በተመለከተ በቅዱስ ሲኖዶስ አማካኝነት ለማከናወን ተስማምተናል። በማለት ይፋዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ከመግለጫው በኋላም ወደ ማረፊያ ቤታቸው ገብተዋል።

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤትም የአባቶችን መመለስ ተከትሎ የጸጥታ ሥራው አስተማማኝ መሆን ይችል ዘንድ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በሕጋዊ መልኩ ጥበቃ ሊደረግለት እንደሚገባ በማመንና ጸጥታውን አስተማማኝ ለማድረግ እንዲሁም የጥበቃ ሥራውን ተቋማዊ በሆነ መልኩ የሚያከናውኑ የፌደራል ፓሊስ አባላት እንዲመደቡለት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ስላገኘ ከፌደራል ፓሊስ ኮሚሽን የፓሊስ አባላት ተመድበው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን የጥበቃ ሥራ እያከናወኑ ይገኛሉ።

በአጠቃላይ በትላንትናው ዕለት የነበረው ሁኔታ ከፍ ሲል በተጠቀሰው አግባብ የተስተካከለ መሆኑን እየገለጽን የተጀመረው የሰላም ሂደት ግቡን ይመታ ዘንድ ምዕመናንና ምዕመናት በወርሃ ጾሙ ወደ ልዑል እግዚአብሔር አጥብቀው በመጸለይ እንዲተጉ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያናችን ጥሪዋን ታስተላልፋለች።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ